Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት ሀገር በማፍረስ ሴራው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተከታታይ ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር የማፍረስ ህልሙን ለማሳካት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተከታታይ ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡

የክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት  እንደገለጹት፥ ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ታጣቂዎችን በማሰማራትና ከሱዳን በመነሳት የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈፀም ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል፡፡

በዚህም የህወሓት ታጣቂ ቡድኖችን በመላክና በሱዳን የሚገኙ ታጣቂዎችን አስርጎ ለማስገባት በክልሉ ላይ ጥፋት አድርሷል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም የጥፋት ፈረሶቹን ይጠቀማል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ሸኔና ሌሎች የጥፋት ተባባሪዎቹ አብረውት መቆማቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጥምረት የጠላትን ሴራ በማክሸፍ ተደጋጋሚ ድል ማስመዝገባቸውን ገልጸው፥ የጥቃት ሙከራዎችም መክሸፋቸውን አቶ አሻድሊ ሀሰን አብራርተዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ በበኩላቸው ክልሉ ከሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጋር ድንበር የሚጋራ መሆኑን እንደምቹ አጋጣሚ በመውሰድ፥  አሸባሪው ህወሓት በውጭ ሀገራት ያሰለጠናቸውን ታጣቂዎች ለማስገባት፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ ላይ እንቅፋት ለመፍጠር እንዲሁም የማዕድን ልማት ሥራን ለማስተጓጎል ፀጥታን ለማወክ ጥረዋል ብለዋል፡፡

ክልሉን ከጠላት እንቅስቃሴ ለመጠበቅ ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች በተጠንቀቅ እንደሚገኙም አመላክተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ህወሓት ከሕዝብ በተቃርኖ መቆሙን ያነሱት የክልሉ አመራሮቹ፥ ለቡድኑ መጠቀሚያ የሚሆኑ ኃይሎች የሰላም አማራጮችን እንዲጠቀሙ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

በአፈወርቅ እያዩ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.