Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት በኮምቦልቻ መጋዘን የተቀመጠውን የእርዳታ እህል መዝረፉ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኮምቦልቻ መጋዘን ያስቀመጠውን የእርዳታ እህል ድራማዊ በሆነ መልኩ መዝረፉ ተገለጸ።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አጣራሁት ባለው መረጃ ቡድኑ ምሽትን ተገን በማድረግ የአካባቢው ሰው በተኛበት ከመጋዘን እህል በመዝረፍ ወደ መቀሌ ማጓጓዙን ገልጿል።

ይሁንና ጠዋት ላይ ድራማ ለመስራት መጋዘኑ በአካባቢው ህዝብ እንደተዘረፈ ለማስመሰል በግዳጅ የአካባቢው ሰው ከመጋዘን እህል እንዲወስድ አድርጓልም ብሏል ኮሚሽኑ፡፡

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ከተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ካትሪን ሶሲ ጋር በአሁናዊ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በዚህ ወቅት መንግሥት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታውን ለማሳለጥ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች ማድረጉን ገልጸዋል።

በሦስት ኮሪደሮች በመጠቀምም ወደ ክልሉ የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀላጠፍ መደረጉን ጠቁመው ከአዲስ አባበ መቀሌ የአየር ትራንስፖርት ተፈቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም አውስተዋል።

የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የጉዞ መረጃ (የይለፍ) ሰነዶች የማዘጋጀትና የኮሙኑኬሽን መሳሪያዎች እውቅና በመስጠት፥ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚያግዝ ገንዘብም ከአዲስ አባበ ወደ መቀሌ ይዘው እንዲሄዱ መደረጉን ጠቁመዋል።

ያም ሆኖ አንዳንድ አካላት የመንግሥትን ጥረት እውቅና ያለመስጠት ችግር ይስተዋልባቸው እንደነበር እና በአንጻሩ ህወሓት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን እየጣሰ ዝምታን መርጠዋል፤ ሲያወግዙትም አይታይም በማለት ተናግረዋል።

ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ይዘው ከገቡት 1 ሺህ 317 የጭነት መኪናዎች መካከል 1 ሺህ 10ሩ ወይም 77 በመቶ የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች እስካሁን አለመመለሳቸውን አስረድተዋል።

እነዚህም ተሽከርካሪዎች የአሸባሪውን ህወሓት አማራና አፋር ክልልን ለመውረር ታጣቂዎችን እያመላለሱ ቢሆንም ቡድኑ በዚህም ድርጊቱ እየተወገዘ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

በቅርቡ ወደ ክልሉ ምግብና ምግብ ነክ ሰብዓዊ ድጋፍ ይዘው የገቡት 203 ተሽከርካሪዎች እስካሁን እንዳልተመለሱም ነው የገለጹት።

ቡድኑ በርካታ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙንና መዝረፉን ጠቁመው በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያም ፈፅሟል ብለዋል።

ሕወሓት በወረራ በያዘባቸው በሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ጎንደርና በዋግኸምራ የሚገኙ ሰዎች ከአምስት ወራት በላይ የሰብዓዊ ድጋፍ አጥተው ሲቀመጡ እነዚህ አከላት ዝምታን መምረጣቸውን አክለዋል።

ያም ሆኖ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ ለማሳለጥ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የሰብዓዊ ድጋፉን ይበልጥ ለማጠናከር ከተመድ ኤጀንሲዎች ጋር ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል።

በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እውቅና መስጠት እንደሚገባና በአሸባሪው ህወሓት የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማውገዝ ከሥምምነት መደረሱን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ በበኩላቸው የተለያዩ የረድኤት ተቋማት የሰብዓዊ ድጋፋቸውን እያሳደጉ መሆኑን ጠቅሰው፥ በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ስፋት ያለው በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብዓዊ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል አሸባሪው ህወሓት በቅርቡ በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘውን የምግብ ማከማቻ መጋዘን መዝረፉን ገልጸው የተዘረፈውም የምግብ መጠን እየተጠና መሆኑን ነው የተናገሩት።

በታሪኩ ለገሰ፤ ተጨማሪ መረጃ ከኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.