Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ በሌሎች ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል – የኦሮሚያ እና አማራ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ በሌሎች ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ሲሆን፥ ኮሚቴው በስብሰባው በወቅታዊ አገራዊ የጸጥታ ጉዳይ እና እየተወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ላይ ተወያይቷል።

የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ርዕሳነ- መስተዳድሮችና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ዶክተር ይልቃል ከፋለ የሽብር ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጠላት መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፥ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሽብር ቡድኑ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘው በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን አውስተዋል።

አሁን ላይ የጸጥታ ኃይሉ ከህዝብ ጋር በመቀናጀት በሽብር ቡድኑ ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ እጅግ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፥ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ህግ የማስከበር እርምጃ መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ጥለው በነበሩ በርካታ ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን አሸባሪው ሸኔ ከሰሞኑ የጸጥታ ኃይሎች በሌሉባቸው አካባቢዎች በመሽሎክሎክ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ማውገዙን ጠቅሰው፥ ኮሚቴው በቀጣይም ህግ የማስከበሩ እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡን አመላክተዋል።

በየትኛውም ክልል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን ያብራሩት ርዕሳነ መስተዳድሮች፥ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ጠብቀው የአገር ጠላት የሆኑ ኃይሎችን በጋራ ሊታገሉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሸባሪው ሸኔ ከሰሞኑን የፈጸመው ጥቃትም ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ለማባላት ያለመ ሴራ መሆኑንም አመላክተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ህብረተሰቡ መንግስት እየወሰደ ላለው ህግ የማስከበር እርምጃ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.