Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት የሚገኘውን የዩኒሴፍ የእርዳታ መጋዘን ዘረፈ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት የሚገኘው ለህጻናትና እናቶች የሚሆን የምግብ ክምችት ያለበትን የዩኒሴፍ የእርዳታ መጋዘን መዝረፉ ተነገረ።

ንጹሀንን በጅምላ የመጨፍጨፍ፣ መንደሮችን የማውደም፣ የእህል ማከማቻዎችን የማቃጠል፣ ተቋማትን የመዝረፍ ወንጀሎችን የቀጠለው አሸባሪው ሕወሃት የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችን መጋዘን መዝረፍ ከጀመረም ውሎ አድሯል።

ኢዜአ ከታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጠው፤ በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት የሚገኘውን የዓለም የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) መጋዘን በአሸባሪ ቡድኑ ዘረፋ ተፈጸሞበታል።

የድርጅቱ መጋዘን ለሕጻናትና ለእናቶች የሚውል ሕይወት አድን የምግብ ክምችት እንደነበረበት ምንጫችን አመልክቷል።

አሸባሪው ሕወሃት በዚህና በተደጋጋሚ በሚፈጽማቸው እኩይ የወንጀል ድርጊቶች ለህጻናትና እናቶች ደንታ እንደሌለው በግልጽ ማሳየቱ ተጠቅሷል።

በተመሳሳይ አሸባሪ ቡድኑ በአማራ ክልል የሚገኘውን የአሜሪካ ተራድኦ ደርጅት (ዩ.ኤስ.አይ.ዲ) መጋዘን መዝረፉን ድርጅቱ ከሰሞኑ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የአሸባሪው ህወሓት አባላት ሰርገው በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ ያሉትን የእርዳታ መጋዘኖቻችን መዝረፉቸው መገለጹ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም በአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ካረን ባስ ባወጡት መግለጫ፤ ዩኤስ አይ ዲ የዕርዳታ መጋዘን በአሸባሪው ቡድን መዘረፉ ክፉኛ እንደረበሻቸው ገልጸዋል።

እርዳታው ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አስቸኳይ ድጋፍ የሚውል እንደነበር ያስታወሱት ባስ፤ አሸባሪ ቡድኑ ድጋፎች ተደራሽ እንዳይሆን ማድረጉን ኮንነዋል።

በተመሳሳይ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ኮሚቴ አባል ሴናተር ጂም ሪሽ የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች የእርዳታ እህል የተከማቸበትን የእህል መጋዘን በመዝረፋቸው ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ሴናተሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ታጣቂዎቹ የዩ.ኤስ.አይ.ዲ መጋዘንን ስለመዝረፋቸው የቀረበው መረጃ እንደረበሻቸው አውስተዋል።

በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤንባሲም በአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል የሚገኙ የዩኤስኤይድ መጋዘኖች መዘረፋቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ማግኘቱን ኢዜአ ዘግቧል ።

የአሸባሪው ታጣቂዎች በገቡባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ሁሉ የእርዳታ መጋዘኖችንና ተሽከርካሪዎችን መዝረፋቸውንና መንደሮችን ማውደማቸውን ለተረጂዎችና ረጂዎቹ እጅግ አሳሳቢ መሆኑ ነው የተነገረው።

የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች የአፋር ክልል ላይ ወረራ በመፈጸም የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ እንዳይገባ ሲያስተጓጉል መቆየቱ አይዘነጋም። በአፋር ክልል ለተፈናቃዮች እርዳታ መጋዘንም ማውደሙም ይታወሳል።

በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት የሚገኘውን በዩኒሴፍ መጋዘን የነበረን የእርዳታ እህል ዘረፋን ጨምሮ በተለያዩ ወቅቶች የሚወጡት መረጃዎችና ማስረጃዎች ሕወሃት የሽብር ድርጊቱን መቀጠሉን የሚያሳዩ ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.