Fana: At a Speed of Life!

አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በመሮጥ የወርቅ ሜዳሊያ ካስገኘ ዛሬ 60ኛ ዓመቱን ያዘ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በመሮጥ የወርቅ ሜዳሊያ ካስገኘ ዛሬ 60ኛ ዓመቱን ያዘ።

የዛሬ 60 ዓመት አበበ ሳይጠበቅ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለመላው አፍሪካ በጥቁር ሕዝብ ታሪክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለማስገኘት በቅቷል።

የሮሙ ድል አፍሪካውያን ሀ ብለው የረጅም ርቀት ውድድሮች የበላይ እንዲሆኑ በር እንደከፈተ ይነገራል።

በወቅቱ አበበ ማራቶኑን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ማይክሮ ሰከንድ የፈጀበት ሲሆን፥ ይህም የዓለም ክብረ ወሰንን በስምንት ሰከንዶች በማሻሻል የዓለም መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል።

በጣልያን አዘጋጅነት በተሰናዳው በዚህ የኦሎምፒክ ውድድር ባልተለመደ መልኩ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ መምጣቱ የሚታወስ ነው።

ይዞ ከመጣቸው አዳዲስ ጉዳዮች መካከል የሮምን የስነ ህንጻ ጥበብ እና ታሪክ ለማሳየት ባለመ መልኩ ዝግጅት ማድረጉ ነው።

እንዲሁም ከዚህ ቀደም በማለዳ ይካሄድ የነበረው የማራቶን ውድድር በሙቀት ምክንያት ወደ ምሽት ነበር እንዲጀመር የተወሰነው።

የማራቶን ውድድሩ ከዚህ በተጨማሪም እንደቀደምቶቹ ውድድሮች የኦሎምፒክ ስታዲየም ተጀምሮ በኦሎምፒክ ስታዲየም የሚጠናቀቅ አልነበረም።

በውድድሩም የማራቶን ተሳታፊዎች የሮም አደባባዮች እና ስነ ህንጻዎች በሚያሳይ መልኩ ውድድራቸውን አካሂደዋል።

ከሌሎቹ ተፎካካሪዎቹ በተለየ ሻምበል አበበ ከራሱ ጋር የታሪክ ትስስር ወዳለው አንድ አደባባይ ሲደርስ ቀና ብሎ መመልከቱ ይነሳል።

ይህም ጣልያን በጦርነት ከወሰደችው የአክሱም ሃውልት የቆመበት ሥፍራ ሲሆን፥ በወቅቱ ፍጥነት መጨመሩም ይነገራል።

የጣልያን ጋዜጦችም የአበበን ድል አስመልክተው ሲዘግቡ የአምስት ዓመቱን ወቅት አስታውሰው ጣልያን ኢትዮጵያን ለማሸነፍ ያሏትን ወታደሮች ሁሉ ስታሰልፍ አንድ ኢትዮያዊ ወታደር ግን ሮምን ድል አደረገ በማለት ዘግበዋል፡፡

አበበ ወደ ኢትዮጵያ ድል አድርጎ ሲመለስ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ እጅ የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ሜዳልያና የአስር አለቃ ሹመት ተቀብሏል፡፡

ሻምበል አበበ ከሮም በኋላ በድጋሚ አራት ዓመታትን ቆይቶ በቶክዮ ማራቶን ክብረ ወሰኑን በማሻሻል ለሀገሩ የወርቅ ሜዳልያ አምጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም የአበበ ቢቂላ 60ኛ የድል ዓመትን በማስመልከት ከሜልበርን እስከ ሪዮ ዲ ጄኔሮ የኦሊምፒክ ባለድሎችን በልዩ መርኃ ግብር ለመዘከር ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ሰሞኑን አሳውቋል።

በአብረሃም ፈቀደ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.