Fana: At a Speed of Life!

አትሌት ማሞ መንግስቱና አትሌት ዝናሽ ጋረደው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድርን አሸነፉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ማሞ መንግስቱና አትሌት ዝናሽ ጋረደው በባህር ዳር ከተማ የተካሄደውን 38ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር አሸነፉ፡፡
በውድድሩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና የባህርዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በወንዶች የማራቶን ውድድር አትሌት ማሞ መንግስቱ ከኦሮሚያ ፖሊስ በአንደኝነት አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አትሌቶች የሆኑት ፅዳት አበጀና አሰፋ ተፈራ እንደየቅደም ተከተላቸው ውድድሩን በ2ኛ እና ሶስተኝነት አጠናቀዋል፡፡
በሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት ዝናሽ ጋረደው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በአንደኝነት አጠናቃለች።
አያንቱ ገመቹ ከፌደራል ፖሊስ 2ኛ ሆና ስትጨርስ÷ አትሌት ብዙአገር አደራ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ 3ኛ ወጥታለች።
በውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች አንደኛ ሆነው ላጠናቀቁ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
2ኛ ለወጡት አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 25 ሺህ ብር፣ 3ኛ ሆነው ላጠናቀቁት ደግሞ 20 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጧቸዋል።
በውድድሩ እስከ ስምንተኛ ለወጡ አትሌቶች እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት መበርከቱን ኢዜአ ዘግቧል ፡፡
በውድድሩ 135 ወንድና 101 ሴት አትሌቶች የተካፈሉ ሲሆን÷ የአንጋፋ አትሌቶች ውድድርም ተካሂዷል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.