Fana: At a Speed of Life!

አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ግድቡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የህብረተሰቡ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የህብረተሰቡ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ጥሪ አቀረበች።

አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ቆይታ አድርጋለች።

በግድቡ ግንባታ ጅማሮ ትልቅ የደስታ ስሜት እንደተሰማት የምትገልጸው አትሌት ደራርቱ፥ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ደግሞ ሌላ ደስታ ሌላ የአሸናፊነት ስሜት እንደፈጠረባትም ትናገራለች፡፡

አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን ወሳኝ የቤት ስራዎችን እየከወነች ነው።

በዚህ ጊዜ ግን ከውስጥም ከውጭም የደህንነት ስጋቶች ተደቅነውባታል።

አትሌት ኮማንደር ደራርቱ በቀጣይ ወራት የሚካሄደውን የውሃ ሙሌት በጉጉት እየጠበቀች መሆኑንም ትገልጻለች።

የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ተምሳሌት ሆኖ እየተጓዘ ያለው የህዳሴ ግድብ አሁን ላይ 80 በመቶ የፕሮጀክት አፈፃፀም ላይ ደርሷል።

በዚህ መካከል ግን በርካታ የደህንነት ስጋቶች ከውስጥም ከውጭም ተጋርጠዋል።

ዝነኛዋ አትሌትም ይህን መሰናክል በአንድነት ከቆምን ማለፍ እንደሚቻል በልበ ሙሉነት ትናገራለች፡፡

አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ አሁን ላይ ከየአቅጣጫው እየተቃጣብን ያለው የደህንነት ስጋት ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በማስቀደም ከተራመድን መቋቋም እንችላለን ብላለች።

ወደዚህ ስኬት ለመድረስ ግን ከትናንት የድል እና የስኬት ታሪኮቻችን ወጣቱ ትውልድ ልምድ መውሰድ ይገባዋል ነው የምትለው።

ታላቁ ወንዝ ዓባይ ለኢትዮጵያውያን የማንነታቸው ማሳያ ትልቁ አሻራ ነውና ህዝቡም የሚያደርገውን ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርባለች፡፡

በስላባት ማናዬ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.