Fana: At a Speed of Life!

አትሌት ወንድወሰን ከተማና እዮብ ኃብተስላሴ አበረታች ቅመሞች በመጠቀማቸው ከውድድር ታገዱ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የስፖርት አበረታች ቅመሞችን (ዶፒንግ) በመጠቀም የህግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ፡፡

አትሌት ወንድወሰን ከተማ ማሞ እና አትሌት እዮብ ኃብተስላሴ ጎሳ የስፖርት አበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) በመጠቀም ተጠርጥረው ጊዜያዊ እገዳ ላይ ሆነው ጉዳያቸው ሲጣራ መቆቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ አበረታች መድሃኒቶች ፅህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በተካሄደው ተጨማሪ ምርመራ አትሌት እዮብ ኃብተስላሴ ጎሳ በፈረንጆቹ የካቲት 2 ቀን 2020 ታይላንድ በተካሄደው ውድድር ላይ Cathinone የተባለውን የተከለከለ የስፖርት አበረታች ቅመም መጠቀሙ ተረጋግጧል፡፡

ስለሆነም አትሌቱ ከፈረንጆቹ ከሚያዝያ 3 ቀን 2020 ጀምሮ ለተከታታይ አራት አመታት በማንኛውም ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡

በውድድሩ የተገኘው ውጤትና ውጤቱን ተከትሎ የሚሰጥ የእውቅና ሽልማትም እንዲሰረዝ ተወስኗል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ አትሌት ወንድወሰን ከተማ ማሞ ቀደም ሲል Cathinone የተባለውን የተከለከለ የስፖርት አበረታች ቅመም መጠቀሙ በመረጋገጡ ከፈረንጆቹ የካቲት 1 ቀን 2024 ድረስ በማንኛውም ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ እገዳ የተጣለበት መሆኑን አስታውሷል፡፡

ይሁን እንጅ አትሌቱ የተሳሳቱ የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ የህግ ጥሰቱን የማጣራት ሂደቱን በተለያየ መልኩ በማስተጓጎልና በድጋሚ ለማጭበርበር በመሞከሩ ተደራራቢ የህግ ጥሰት በመፈፀም ተጠርጥሮ ጉዳዩ ሲጣራ ቆይቷል ነው የተባለው፡፡

በመሆኑም አትሌት ወንድወሰን ያቀረባቸው ሰነዶች የሐሰት መሆናቸው በመረጋገጡና በፀረ-ዶፒንግ ህጉ አንቀፅ 2 ነጥብ 5 ላይ የተደነገገውን የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴ የማስተጓጎልና አቅጣጫ የማሳት የህግ ጥሰት መፈፀሙ በመረጋገጡ ቀደም ሲል ከተጣለበት የአራት አመት የእገዳ ቅጣት በተጨማሪ የመጀመሪያው ቅጣት ከሚያበቃበት የካቲት 1 ቀን 2024 ጀምሮ ለተከታታይ ስምንት አመታት እስከ የካቲት 1 ቀን 2032 በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ የእገዳ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅህፈት ቤት በቀጣይም የምርመራና ቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቀው፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.