Fana: At a Speed of Life!

አቶ ስብሀት ነጋን ጨምሮ እስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ተገቢ በሆነ መንገድ እየተስተናገዱ ነው – ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ እስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ተገቢ በሆነ መንገድ እየተስተናገዱ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

ከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎችን አያያዝ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በመገኘት በታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል አድርገዋል፡፡

በጉብኝቱ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙትን እነ ዶክተር አብረሀም ተከስተ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አቶ ስብሀት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ዶክተር አዲስ አለም ባሌማ፣ ሜ/ጀኔራል ይርዳው ገብረ መድኅን፣ ሜ/ጀኔራል ገብረ መድኅን ፍቃዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ታሳሪዎች የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ ጎብኝተው ታሳሪዎችን አነጋግረዋል።

እንዲሁም ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎች ንፁህ እና ብዙም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው መሆኑንና አጠቃላይ ሁኔታው ተቀባይነት ያለው መሆኑንም ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡

ሁሉም ከላይ የተጠቀሱት ታሳሪዎች ወደ ፌዴራል ፖሊስ እስር ቤት ከመጡ ወዲህ ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የህክምና አገልግሎት ባለው አቅም እያገኙ እንደሆነ፣ ከቤተሰባቸው ተገናኝተው አቅርቦት እንደሚቀበሉ እና ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

የተወሰኑ ታሳሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል በበረሀ ውስጥ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በሰብአዊ እንክብካቤ መያዛቸውን እና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከድንገተኛ አደጋና ጥቃት እንደጠበቋቸው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ በትግራይ ክልል ከመቐለ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ተኩስ እንደነበረና የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው፣ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብ እና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ ያነሱ ታሳሪዎች እንዳሉ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የተጠረጠሩበት ጉዳይ  በተናጠል አለመቅረቡን እና የምርመራ ሂደቱ  በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል።

ታሳሪዎቹ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከጠበቆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ማጠሩን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የተወሰኑ ታሳሪዎች የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ የሚገኙበት የአያያዝ ሁኔታ በተገቢው ደረጃ መሆኑን በማረጋገጥ፣ በታሳሪዎች የተነሱ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች ላይ ከእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል፡፡

ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የወንጀል ምርመራውን በተቻለ ፍጥነት ማጠናቀቅ እና የሕግ አግባብ በሚፈቅደው መልኩ በዋስትና ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች መለየት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.