Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ለ1442ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለ1442ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ታላቁ የረመዳን ፆም በአማኞቹ ዘንድ ልዩ ሃይማኖታዊ ትርጉም ያለው ሲሆን፤ በአንድ ወር የፆም ፀሎት ጊዜ ከዕምነቱ ውጪ ያሉ ወገኖቻችንን ጋር አንድነታችንን ይበልጥ ለማጥበቅ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነበር ብለዋል።

መልካም አጋጣሚዎችን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ የኢፍጠር መርሃ ግብሮች ላይ ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን ማዕድ የተጋራንባቸው መድረኮች የአብሮነታችን ውሃ ልክ ትክክለኛ ማሳያዎች ነበሩም ነው ያሉት።

በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን አንድነታችንን ይበልጥ የሚያጠብቁ እና የሚያደምቁ መርሃ-ግብሮችን ሃገራዊ መሠረት እና ይዘት እንዲኖራቸው የበለጠ መስራት ይጠበቅብናልም ብለዋል በመልዕክታቸው።

”ባሳለፍናቸው ጊዜያት በዜጎቻችን ላይ ያጋጠሙ አሳዛኝ ጥፋቶች እንዳይደገሙ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ከውስጥ እና ከውጭ ከገጠመን ፈተና በጥበብ ለመሻገር በፅናት መረባረብ ይኖርብናል” ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በተለየ የዜጎቿ ደህንነት እንዲጠበቅ፣ አንድነታቸው እንዲጠናከር እና እንዲደምቅ የሻተችበት ወቅት ላይ እንገኛለንም ነው ያሉት።

ይህ ታሪካዊ የለውጥ ጉዞ በልዩነቶቻችን ላይ ቆሞ ከመሳሳብ ይልቅ፤ አንድነታችንን በሚያፀኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ተጎጂ ወገኖችን የመደገፍና ዘላቂ ሰላም እውን ማድረግ ቀዳሚው ኃላፊነታችን ይሆናልም ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በታላቁ የረመዳን ወር ከአንድነታችን የሚቀዳው መደጋገፍ፣ መተሳሰብ እና መረዳዳት ኢትዮጵያዊ መሰረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.