Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተመራው የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ ፔካ ሀቪስቶ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ትግራይ ክልል የሚሰያስፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የኢትዮጵያ መንግስት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍን መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን ለ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን አቶ ደመቀ አስታውሰዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ ቀደም ሲል ሲተገበር የነበረው የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም የተጀመረ መሆኑን የገለፁጽት አቶ ደመቀ ይህም በክልሉ ሁኔታዎች ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሱ ስለመሆኑ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ ከማደረግ አንጻር የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቀደም ሲል በማይካድራ እንዲሁም በመቀጠልም በአክሱም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ በማድረግ ያቀረበውን ሪፖርት አስታውሰው በመንግስት በኩል በገለልተኛ አካላት አማካይነት ምርመራ እንዲደረግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል።
ፔካ ሀቪስቶ በበኩላቸው ከሁለት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተደራሽነትና የሚዲያ አካላት በክል በመገኘት እንዲዘግቡ ከማድረግ አንጻር በመንግስት የተከናወኑ ተግባራት በአዎንታዊነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ያደረጉት ጉብኝትም ይህንን የሚያረጋግጥ መሆኑን ያነሡ ሲሆን ግጭት ያለባቸው የተወሰኑ አካባቢዎች እርዳታ የሚያስፈለጋቸው ዜጎች ተገቢው እርዳታ እንዲደርሳቸው ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ሀቬስቶ አያይዘውም የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች በክልሉ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው ለተደራሽ አካላት ተገቢው ድጋፍ ማቅረብ እንዲቻል የፍላጎት አጠቃላይ ዳሰሳ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ አንዲሚወጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸው በአዎንታዊነት እንደሚገነዘቡት ገልጸው ሂደቱ እንዲፋጠን ጠይቀዋል።
አቶ ደመቀ በበኩላቸው በመንግስት በኩል በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ከመጪው የዝናብ ወቅት በፊት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም አንዲቻል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤርትራ ወታደሮች አንደሚወጡ በገለጹት መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱ እንዲፋጠን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በወንጀል ከተሰማሩ የተለዩ ዋና የህወሓት ቅሬቶች ውጭ ሌሎች አካላት በፈቃደኝነት ለመንግስት እጅ እንዲሰጡ የምህረት ገደብ ማውጣቱ አስታውሰው በዚሁ መሰረት እጃቸውን ለመንግስት ያልሰጡትን ወደ ህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተም ኢትዮጵያ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ድርድሩ በውጤት አንዲጠናቀቅ ላደረጉት ጥረት ኢትዮጵያ ከበሬታ ያላት መሆኑን አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
በቀጣይም በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ድርድሩ በአውሮፓ ህብረት፣ በአሜሪካ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ታዛቢነት እንደሚካሄድ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ በኩል በውሃ ክፍፍል ስምምነት በሶስቱ አገራት መካከል ብቻ የሚካሄድ አለመሆኑን እንዲሁም ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ገልጸው ድርድሩ በግድቡ የውሃ ሙሌት ላይ ማተኮር እንዳለበት አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
ሀቬስቶ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ድርድር ከመጪው ክረምት ከሚከናወነው የውሃ ሙሌት በፊት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው በአውሮፓ ህብረት በኩልም የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮ-ሱዳንድ የድንበር ውዝግብን ሁለቱ አገራት በድርድር መፍታት ያለባቸው መሆኑን ሀቬስቶ አንስተዋል።
አቶ ደመቀ በበኩላቸው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሱዳን የኢትዮጵያን ልዑላዊ መሬት በወረራ መያዟን ተከትሎ ማውገዝ የሚጠበቅበት ቢሆንም ይህንን አለማድረጉ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸው በኢትዮጵያ በኩል ችግሩ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ጽኑ አቋም ያለ መሆኑን ማስረዳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.