Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር ቦሪታ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸው ወቅትም የሃገራቱን የሁለትዮሽና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መክረዋል፡፡

አቶ ደመቀ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በህዳሴ ግድብ፣ በኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ እና ከመጪው ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ገለጻ አድርገዋል፡፡

አያይዘውም ሃገራቱ በሞሮኮው ንጉስ ሞሃመድ 4ኛ ጉብኝት ወቅት ለተፈራረሟቸው የመግባቢያ ስምምነቶች ተግባራዊነት መስራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በሃገራቱ የጋራ ጥምረት የሚገነባውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ወደ ስራ ማስገባትና ሃገራቱን በቀጥታ የአየር ትራንስፖርት ማስተሳሰር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በተመለከተ አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ሞሮኮ ለተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተርነት ለሚወዳደሩት ዶክተር አርከበ ዕቁባይ ድጋፍ እንደምትሰጥ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡

የሞሮኮው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር ቡሪታ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው፥ ኢትዮጵያ ድንበሯንና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት ሃገራቸው ትደግፋለች ብለዋል፡፡

ከህዳሴው ግድብና ከኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘም፥ በሁሉም አካላት በኩል ሰላማዊ የሆነ መፍትሄ እንደሚደረስ እምነታቸው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

አያይዘውም በሃገራቱ መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.