Fana: At a Speed of Life!

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ከሚገኙት የኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሃም ሳንግ ውክ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይቱ አቶ ገዱ ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ያላቸው ግንኙነት በሀሉም መስክ ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በደም የተሳሰረ መሆኑንና ይህንን ግንኙነት ይበልጥ በህዝብ ለህዝብና አቅም ግንባታ ዘርፍ ለማጠናከር ኢትዮጵያ እንደምትሰራም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ኮሪያ እያደረገች ላለው ድጋፍም አቶ ገዱ ምስጋና አቅርበዋል።

የኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሃም ሳንግ ውክ በበኩላቸው በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል፡፡

በሌላ በኩል ከደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ዩንግ ውሃ የተላከን መልዕክት ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስረክበዋል።

በኮሪያ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በመላከ ስላደረገችው ድጋፍ ማመስገናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረገች ያለውን የተሳከ ጥረት ኮሪያ እንደምታደንቅና ሃገራቸው ኢትዮጵያ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለምታደርገው እንቅስቃሴ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋገጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.