Fana: At a Speed of Life!

አንድነትና ሰላምን ለማረጋገጥ ክላሽና ታንክ ሳይሆን የሚያስፈልገው ልማትን ማረጋገጥ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም ለማረጋገጥ ክላሽና ታንክ ሳይሆን የሚያስፈልገው ልማትን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ለነዋሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ካለንበት ድህነት ለመውጣት ጦርነት ሳይሆን ልማትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድህነት ስላለ ትራክተር፣ አለመማር ስላለ ትምህርት ቤት እንዲሁም በሽታ ስላለ የጤና ተቋም ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ሰላም፣ አንድነትን እና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በጋራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የስልጤን ህዝብ ታታሪነትና ስራ ወዳድነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ታዳጊዎችን ክላሽ ማሸከም ጦርነትን ማውረስ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም የህዝብ ተቀባይነትን ለማግኘት ከሚደረግ ሸፍጥ ወደ ሃቅ መሸጋገር እንደሚገባ ጠቅሰው፥ ባለፉት 27 አመታት ከነበረው መስመር አሁን ወደ ብልጽግና ጎዳና ገብተናልም ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

መንግስታቸው ዕዳ ያለባትን ሃገር እንደመረከቡም ሃገሪቱን ወደ ብልፅግና ለማድረስ እንቅልፍ አይኖረውም ብለዋል፤ ከሃገር ድህነት በላይ ዕዳ እንደሌለ በመጥቀስ።

አያይዘውም ድህነትን በማሸነፍ የሃገሪቱን ዕዳ እንከፍላለንም ነው ያሉት።

ድህነትን ማሸነፍ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ባለመሆኑም መላው ህብረተሰብ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ከስልጤ ዞን ነዋሪዎች የሚነሱ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችም ሙሉ በሙሉ በደረጃ እንደሚፈቱም አስረድተዋል።

በአላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.