Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ ላይ እየወጣ ያለው የሐሰት ዘገባ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና አካል ነው- አቶ አባዱላ ገመዳ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29 ፣2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሲኤንኤን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ እያወጣው ያለው የሀሰት ዘገባ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ዓለም አቀፍ ጫና አካል መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ ገለጹ።
አቶ አባዱላ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፥ ሲኤንኤን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ እያወጣ ያለው ዘገባ ውሸትና የተዛባ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ህጎችን አክብሮ የሚሰራ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፥ አየር መንገዱን በተመለከተ እየወጣ ያለው የተዛባ ዘገባ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ዓለም አቀፍ ጫና አካል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ መለያ ዓርማ ሆኖ የሚያገለግል ትልቅ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው ያሉት ቦርድ ሰብሳቢው፥ ዘገባው የኢትዮጵያ መለያ እና ኩራት የሆኑ ተቋማትን በማጠልሸት ከገበያ ለማስወጣት የሚያደርጉት ጥረት አካል ነው ብለዋል።
እንደ አቶ አባዱላ ገለጻ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ህጎችን አክብሮ የሚሰራ ተቋም ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትም አየር መንገዱን ከዓለም አቀፍ የአየር መንገዶች እንቅስቃሴ ውጭ የተጠቀመበት አንዳችም አካሄድ እንደሌለ አስታውቀው፤ ከሚገምቱት በላይ ውጤታማ በመሆኑ መልካም ስሙን አጠልሽተው ወደኋላ ለመመለስ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ አባዱላ እንዳብራሩት በኮቪድ 19 ወቅት የመንግሥትን ድጎማ ያልጠየቀ አየር መንገድ የለም ያሉት ቦርድ ሰብሳቢው፤ ብዙዎች ሥራ ሲያቆሙ አንዳንዶች ሠራተኛ ቀንሰዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በዛ አስቸጋሪ ጊዜም በውጤታማነቱ ቀጥሏል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.