Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ የስኬት ተሞክሮውን ለሌሎች ተቋማት እንዲያካፍል ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ ያደረጉትን ሚስጥሮች በሌሎችም ትላልቅ የአገሪቱ ፕሮጀክቶች ላይ መድገም ይቻል ዘንድ ተሞክሮውን እንዲያሰፋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዛሬው እለት ግንባታው እየተጠናቀቀ የሚገኘውን የመንገደኞች ማስተናገጃ (ተርሚናል) ጨምሮ የተለያዩ የአየር መንገዱ የሥራ እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት፤ የአየር መንገዱ የአፍሪካና የዓለም ኩራትነቱን አጠናክሮ መቀጠል መቻሉን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ይህ ታላቅ ስኬት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በሚያንቀሳቅሱ የሀገሪቱ የተለያዩ የልማት ተቋማት ላይም መጠቀም ይቻል ዘንድ የስኬት እውቀቱ ወደሌሎችም የሚተላለፍበትን መንገድ አየር መንገዱ እንዲዘይድ አፈ ጉባኤው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በበኩላቸው ኩባንያው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 2025 ድረስ ለማሳካት ይዞት የነበረውን ህልም ከወዲሁ እውን ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትጵያ አየር መንገድ ደንበኞችን በማጓጓዝም ሆነ በካርጎ ጭነት ማመላለስ በአፍሪካ ከሚገኙ አየር መንገዶች ሁሉ ቀዳሚው እንደሆነ ጠቁመዋል።

አክለውም አየር መንገዱ በተጠናቀቀው የአውሮፓዊያን ዓመት 12 ሚሊየን መንገደኞችንና ከ432 ሺህ ቶን በላይ ዕቃዎችን አጓጉዟል ሲሉም አስረድተዋል።

በዚህ አገልግሎቱም በዓመቱ አራት ቢሊየን ዶላር ማስገባት መቻሉንም ይናገራሉ።

በማንኛውም የፖለቲካ ሁኔታ ጣልቃ አለመግባቱ፤ እስከ አሁን ሀገሪቱን የመሩ መንግሥታትም በአየር መንገዱ አሠራር ላይ ጣልቃ አለመግባታቸው አየር መንገዱ ስኬታማ እንዲሆን ካስቻሉት ምክንያቶች መካከል ናቸው ብለዋል።

የማኔጅመንቱ ተጠያቂነትንና ግልጸኝነትን መሰረት ያደረገ የአሠራር ሥርዓት መከተሉም ለስኬቱ ቁልፍ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በአየር መንገዱ የአሠራር ሥርዓትና የስኬት ሚስጥር ላይ ጥያቄና ማብራርያ ጠይቀው ከዋና ሥራ አስፈጻሚው መልስ ተሰጥቶባቸዋል።

ምክር ቤቱ አየር መንገዱ ለያዘው ቀጣይ ስኬት እውን መሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አባላቱ ቃል ገብቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት አህጉራት ከ127 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ላይ የሚበር ሲሆን፤ በሳምንት ከ2 ሺህ በላይ መንገደኞችን ያስተናግዳል፤ በየቀኑ ደግሞ ከ300 በላይ በረራዎችን እንደሚያደርግም በዚሁ ጊዜ ተጠቅሷል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.