Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ የብር ኖት መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ46 ቢሊየን ብር በላይ መሰራጨቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 1 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)አዲሱ የብር ኖት መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ46 ቢሊየን ብር በላይ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የግል ባንክ ቅርንጫፎች መሰራጨቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብሔራዊ ባንክን በመወከል አዲሱን የብር ኖት ለግል ባንኮች ጭምር በማሰራጨት ላይ መሆኑን የባንኩ ፕሬዜዳንት አቶ አቤ ሳኖ ገልጸዋል።
በዚህም አዲሱን የብር ኖት ማሰራጨት ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ከ46 ቢሊየን ብር በላይ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የግል ባንክ ቅርንጫፎች መሰራጨቱን ጠቁመው÷ከዚህ ውስጥ 28 ቢሊየን ብር ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች መሰራጨቱን ገልፀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ 22 ቢሊየን አሮጌው የብር ኖት ወደ ማዕክል ገቢ መደረጉንም አቶ አቤ ጨምረው ገልፀዋል።
አምስት ሺህ ብር እና ከዛ በላይ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብር ለመለወጥ የሚመጡ ደንበኞች የብሔራዊ ባንክ መመሪያ በሚያዘው መሠረት በቁጥር ስልሳ ሦስት ሺህ ደንበኞች አዲስ የባንክ አካውንት መክፈታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከ 6 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ መቆጠቡንም አቶ አቤ አስረድተዋል።
አዲሱን የብር ኖት በብር መክፈያ ኤቲኤም ማሽኖች ለመክፈል አዲሱን ብር እንዲለምዱ ከማድረግ አኳያም በርካታ ሥራዎች መሠራቱንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ 3 ሺህ 700 ኤቲኤም ማሽኖች በሙሉ ማለት በሚያስችል ደረጃ አዲሱን የብር ኖት እንዲከፍሉ የማድረግ ሥራ መሰራቱንም የባንኩ ፕሬዘዳንት ገልፀዋል።
ከመቶ ሺህ ብር በላይ ለሚቀይሩ ደንበኞች በቀሩት 5 ቀናት ውስጥ ሰንበትን ጨምሮ በመስራት ላይ ወዳሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በመምጣት በቀነ ገደቡ እንዲጠቀሙ አቶ አቤ ማሳሰባቸውን ከንግድ ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.