Fana: At a Speed of Life!

አዲስ ወግ “ከጽንፎች መካከል ወርቃማውን አማካይ ፍለጋ”በሚል ርዕስ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስሴክሬታሪያት የሚዘጋጀው የሩብ ዓመቱ አዲስ ወግ ዐቢይ ጉዳይ “ከጽንፎች መካከል ወርቃማውን አማካይ ፍለጋ” በሚል ርዕስ እየተካሄደ ነው፡፡

በጽንፈኝነት ፍቺ እና ዐውድ ላይ ያተኮረው የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድሙ ገለፃ አቅራቢነት እና በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አዘጋጅ ፀጋ ታሪኩ አመቻችነት መካሄድ መጀመሩን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ፕሮፌሰር ሀብታሙ በገለጻቸው÷ ጽንፈኝነት በሕብረተሰቡ ውስጥ አለመረጋጋትን፣ አለመተማመንንና አለመተባበርን ይፈጥራል፤ በዚህም ሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ይስተጓጎላል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ በአጠቃላይ፣ መንግስት፣ ትምህርት ቤቶች ሚዲያ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ለሰላምና ለአገር አንድነትና ዕድገት የቆሙ ኃይሎች በሙሉ ጽንፈኝነትን ለማስወገድ ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን መፈጸማቸው ተገቢ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥዋል፡፡

ዶክተር ቃለአብ ታደሰ በበኩላቸው÷የራሱን አስተሳሰብ ለራሱ የሚያራምድ ለዘብተኛ አጥባቂ፣ ወደ ሌሎች አስተሳሰቡን በሕጋዊ መንገድ ለማጋባት የሚሻ አመክንዮአዊ አጥባቂ መኖሩን አንስተው÷ችግር ፈጣሪው በግድ አስተሳሰቡን ሌሎች ላይ ለመጫን የሚሻው አጥባቂ ነው ብለዋል፡፡

ዶክተር ጌታነህ መሐሪ ፖለቲካችን በአብዛኛው ብሔር ተኮር መሆኑን ጠቁመው÷የብሔር ማንነት ከመልክዓምድርና ቋንቋ ጋር የተያያዘ መሆኑ ወገናዊነትን የመያዝ ዝንባሌ እንደሚያስከትል አብራርተዋል፡፡

በፖለቲካው ይህን እንደ መሣሪያ ተጠቅሞ ሰዎች ራሳቸውን የበላይ አድርገው እንዲያዩ እና እንደ ተጠቂ ራሳቸውን የሚቆጥሩ እንዲሆኑ እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡

የባህልና የቋንቋ ብዝሃነት አውነታ መሆኑን መቀበል፣ ትስስርና ተመሳስሎ እንዳላቸው ልብ ማለት ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ጌታነህ÷ኢ ፍትሐዊነትን በማንኛውም ሁኔታ መታገል እንደሚያስፈልግ አውስተዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ÷ ሁሉን አሳታፊ ተግባቦት እርስ በርስ ወደ መግባባት ያመጣል፤ ለዚህም መርሐ ግብሮችን ከሁሉም እሳቤ አንጻር መቅረጽ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በዘመቻ መልክ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በዕቅድ የመገናኛ ብዙሃን የጋራ ፎረም ኖሮ በጽንፈኝነት ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሠራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.