Fana: At a Speed of Life!

አዲስ ዓመትን ተከትሎ የአትክልትም ሆነ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እጥረት እንደማይኖር ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 28 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)አዲስ ዓመትን ተከትሎ የአትክልትም ሆነ የሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች የአቅርቦት እጥረት እንደማይኖር የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተወጣጣ ቡድን በመዲናዋ የአትክልትና ፍራፍሬ እንደሁም የመሰረታዊ ሸቀጥ አቅርቦትን በተመለከተ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የልኡካን ቡድኑ በጉብኝቱ የስኳር አቅርቦትን ጨምሮ የአትክልት ፍራፍሬ እንዲሁም የሌሎች ፍጆታዎች አቅርቦት የተሟላ መሆኑን አረጋግጧል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ÷ በአዲስ ዓመት የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይኖር ከወዲሁ ተሰርቷል ብለዋል ።

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የአትክልትና ፍራፍሬ እጥረት እንዳይኖር በሁሉም መደብሮች በቂ አቅርቦት መኖሩንም ጠቁመዋል።

የግብይት ሰንሰለቱ ጤናማ እንዲሆን እና የምርት መደበቅም ይሁን መሰወር እንዳይኖር ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከፍተኛ ፋላጎት እንደሚኖር በማሰብም ከዘመን መለወጫ በዓል ቀደም ብሎ ፍልጎትን መሠረት ያደረገ የአቅርቦት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በመንግስት በኩል አንዳንድ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ተመቻችቷል ያሉት አቶ ወንድሙ÷ በዚህም በዘይት እና ሌሎች ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቅናሽ መታየቱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የአቅርቦት ክትትልና ዌር ሃውሲንግ ቡድን መሪ አቶ ደሣለኝ ተሠማ በበኩላቸው÷ አሁን ላይ በቂ ሊባል የሚችል የስኳር አቅርቦት አለ ብለዋል።

ከውጪ ገበያ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ግዢ ተፈፅሞ እስካሁን 900 ሺህ ኩንታሉ አገር ውስጥ ገብቶ በመጋዘን የሚገኝ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ቀሪው ስኳርም በመጓጓዝ ላይ በመሆኑ በቅርቡ አገር ውስጥ እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.