Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ለተጀመረው እንቅስቃሴ አፍሪካውያን እንዲቀላቀሉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖረው የተጀመረው እንቅስቃሴ የነጻነት፣ የእኩልነትና የፍትሐዊነት ትግል በመሆኑ አፍሪካውያን መቀላቀል እንዳለባቸው በአሜሪካ ስቶኒብሩክ በሚገኘው የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ፖለቲካና ታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ሽመልስ ቦንሳ ገለጹ።
አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ የተጀመረው እንቅስቃሴ አዲስና ፍትሐዊ ዓለም የመፍጠር ትግል አካል መሆኑን ነው ለኢዜአ የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን ከሁለንተናዊ ጫና ነጻ የማውጣት ትግሉን በተጠናከረ መልኩ በማካሄድ በአፍሪካ ያላትን ታሪካዊ ስፍራ ይዛ መቀጠል እንዳለባትም አስገንዝበዋል።
አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለው ጥያቄ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ መሰረት ያለው መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ሽመልስ÷ የአፍሪካ የነጻነት አባቶች አህጉሪቱ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ማግኘቱ የፍትሐዊነትና እኩልነት ጥያቄ መሆኑን በማስታወቅ ትግል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አሁንም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ሌሎች የአህጉሪቱ መሪዎች ጥያቄውን ማንሳታቸው ከፍትሃዊነትና ከእኩልነት የመነጨ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት ሲቋቋም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊዎችን ፍላጎት የማስጠበቅ አላማ የነበረው የተቀረውን ዓለም የማይወክል እንደሆነ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የነጻነት አባቶች የተጀመረው ትግል አሁን እንደ አዲስ መቀስቀሱ ትግሉን በዓለም ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ውጤታማ ሊያደርጉት የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ሰአት የዓለም የፖለቲካ አሰላለፍ በመቀየሩ ምክንያት ብዙ የኃይል ስብስቦች በመፈጠራቸው ጥያቄው ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
አፍሪካውያን በአሁኑ ሰአት የራሳችንን እጣ ፈንታ በራሳችን መወሰን አለብን በሚል ለፍትሐዊነትና ለእኩልነት እያደረጉት ያለው አዲስ ትግል የምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንቅስቃሴውን እንዲቀጣጠል የሚያደርግ መሆኑንም አመልክተዋል።
“የተጀመረው እንቅስቃሴ በምዕራባውያን ፍልስፍና የተቃኘውን የዓለም አካሄድ በመቀየር አዲስና ፍትሐዊ ዓለም የመፍጠር ትግል አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለውን እንቅስቃሴ መቀላቀሏ በታሪክ በአፍሪካውያንና በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ካላት ተቀባይነት አንጻር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው” ብለዋል ዶ/ር ሽመልስ።
ኢትዮጵያ አፍሪካን ነጻ ለማውጣት የጀመረችው ትግልም ለአፍሪካውያንና ለሌሎች የተጨቆኑ ሕዝቦች መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ትግሉን በተጠናከረ መልኩ በማካሄድ በአፍሪካ ያላትን ታሪካዊ ስፍራ ይዛ መቀጠል እንዳለባትና ይሄን ካደረገች አፍሪካውያንን አንድ የማድረግ አቅም እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አፍሪካ የሚገጥሟትን ፈተናዎች መቋቋምና መሻገር የምትችልባቸውን አማራጮች የቃኘ አፍሪካ ተኮር የሆነ የውጭ ፖሊሲ ልትቀርጽ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አፍሪካውያን በነጻ የንግድ ቀጠና ጨምሮ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ለመዋሃድ የጀመሩት እንቅስቃሴ የጋራ ራዕይ እንዲፈጠር የማድረግ ጥቅም ስላለው በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.