Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ እና ሩሲያ ባህላዊ ትስስራቸውን መልሰው በመገንባት ወዳጅነታቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ እና ሩሲያ ባህላዊ ትስስራቸውን መልሰው በመገንባት ወዳጅነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ “የሩሲያ-አፍሪካ፣ ባህልን መልሶ መገንባት” በሚል መሪ ሃሳብ  በተካሄደው አለም አቀፍ የፓርቲዎች ጉባኤ ላይ በበይነ መረብ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም “ባህላዊ ትስስርን መልሶ በመገንባትና ወዳጅነታችን በማጠናከር እንዲሁም በጊዜ ሂደት የተፈተነውን አብሮነት በማጽናት የህዝቦችን መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አካላትን መመከት ያስፈልጋል” ብለዋል።

ጉባኤው መሪ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ ፖለቲካ መረጋጋትና ለአለም አቀፍ ትብብር ያላቸውን ሚና በግልጽ የሚያሳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሩሲያ ፌዴሬሽን የበርካታ ፈላስፎች መኖሪያ መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህም ለአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ህዝባቸው ነጻ የሆነችና በኢኮኖሚ የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር ህልም አንግበው እንዲነሱ መነሳሳት ፈጥረውባቸዋል ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግስትን አስተዳደር የተመለከቱ የፍልስፍና አስተምሮቶችን በመከተል በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ዛሬ ላይ ሁሉም በእውነት ላይ የተመሰረተና ግለሰባዊ ብቃትንና የጋራ የሆነ መልካም ስብዕናን ለመፍጠር የሚያስችል ውጤታማ የሆነ የፍልስፍና እሳቤ ለማራመድ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡

“እኔም ይህንን እሳቤ የሚያራምደውን የብልጽግና ፓርቲ በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ እገኛለሁ“ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

እንደ አጠቃላይ አፍሪካ እና ሩሲያ ባህላዊ ትስስራቸውን መልሰው በመገንባት ወዳጅነታቸውን በማጠናከር የህዝባቸውን ጥያቄ መመለስ አለባቸው ብለዋል።

የተባበሩት የሩሲያ ፓርቲ ጄኔራል ካውንስል ምክትል ፀሐፊና የሩሲያ ፌዴሬሽን ሴናተር ኪልሞቭ አንደሬይ በበኩላቸው የጉባኤው ትኩረት በዝግጅቱ ላይ በሚቀርቡ ርዕሶች፣ በሰላምና ደህንነት ፣ ጣልቃ ገብነትን በመመከት ላይ ያተኩራል ብለዋል፡፡

ሩሲያ ኮቪድ 19ን በመከላከል ረገድ ልምዷን ለማካፈልና ክትባቱን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

እኤአ በሰኔ 2010 “ሩሲያ አፍሪካ፣የትብብር አድማስ” በሚል መሪ ሃሳብ በሞስኮ አለም አቀፍ የፓርላማዎች ጉባኤ መካሄዱንም አስታውሰዋል።

የዛሬው ጉባኤ በተባበሩት የሩሲያ ፓርቲ አማካኝነት መዘጋጀቱ ታውቋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.