Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ የኃይል አቅርቦት እጥረቷን ለመቅረፍ ወደ ኒውክሌር የኃይል አማራጭ ማማተር አለባት ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለማችን የነዳጅ እና የኃይል አማራጭ ኢንዱስትሪዎች እያደጉ ቢመጡም አፍሪካ ግን እስከ አሁን በኃይል አቅርቦት እጥረት መመታቷ ነው የተገለጸው፡፡

ከ600 ሚሊየን በላይ የአፍሪካ ህዝቦች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደማያገኙ እና በጨለማ እንደሚኖሩም ነው የተመለከተው፡፡

አፍሪካን ከድህነት አረንቋ ለማላቀቅ የኒውክሌር የኃይል አማራጭን መጠቀም የግድ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ምንም እንኳን አፍሪካ በነዳጅ ምርቷ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታዩ ባሉ የታዳሽ ኃይል መርሃ – ግብሮቿ እመርታ ያሳየች ቢሆንም አህጉሯ የሚያስፈልጋትን ዘላቂ የኃይል አቅርቦትለመሸፈን እጅግ እንደሚቀራት ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

በመሆኑም የአፍሪካውያን ቁጥር ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎቶቻቸው መጨመር መሳለመሳ የሀገራቱ የፍጆታ ክፍያም እየጨመረ መምጣቱ ነው የተገለጸው፡፡

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን በተለያዩ የኃይል አማራጮች ለመሸፈን ቢሰሩም የኒውክሌርን የኃይል አማራጭ ለመጠቀም ግን በጣት ከሚቆጠሩ ሀገራት በስተቀር እምብዛም አልደፈሩም ነው ያለው አፍሪካ ፖሊሲ ሪቪው፡፡

እንደ ደቡብ አፍሪካ ፣ ግብጽ እና ኬንያ ያሉ ሀገራት የኒውክሌር ኃይልን የኤሌክትሪክ ፍላጎታቸውን ለማሟላትም እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ጠቅሷል፡፡

ግብጽ ከፈረንጆቹ 1954 ጀምሮ ኤል ዳባ ከተሰኘው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዋ 4 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ያህል የኃይል ፍላጎቷን እንደምትሸፍንም ነው የተመለከተው፡፡

ኬንያ የዜጎቿን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት እየገነባች የምትገኘው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫም በፈረንጆቹ 2027 እንደሚመረቅም አፍሪካ ፖሊሲ ሪቪው አመልክቷል፡፡

ዩጋንዳም አይኗ የኒውክሌር የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭን ማማተር ከጀመረች እንደቆየች እና በፈረንጆቹ 2019 “ሮሳቶም” ከተሰኘ ኩባንያ ጋር እንደተፈራረመች ነው የተጠቆመው፡፡

ሴኔጋልም ለዘርፉ ፍላጎቷን አሳይታለች ነው የተባለው፡፡

ሀገራት የኒውክሌር ኃይልን በአግባቡ ከተጠቀሙ ከአካባቢ ብክለት ነጻ፣ የማይቆራረጥ እና በአነስተኛ ዋጋ ለዜጎች ማከፋፈል የሚቻል የኃይል አማራጭ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ አፍሪካ ከህዝብ እድገቷ አንጻር ከፍተኛ የኒውክሌር ኃይል አቅርቦት ማዳረስ የሚያስችል ግንባታ ለማከናወን በርካታ ዓመታትን የሚወስዱባት ቢሆንም የአህጉሯ ሀገራት እስከ 300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸውን አነስተኛ የኒውክሌር ማበልጸጊያዎች በመገንባት የህዝቦቻቸውን ፍጆታ ለማቃለል መሥራት እንዳለባቸው አፍሪካ ፖሊሲ ሪቪው ምክረ-ሃሳቡን አስቀምጧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.