Fana: At a Speed of Life!

ኢራን የዩክሬንን የመንገደኞች አውሮፕላን መታ መጣሏን አመነች

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢራን የዩክሬንን የመንገደኞች አውሮፕላን “በተፈጠረ ስህተት” መታ መጣሏን አመነች።

ቴህራን አውሮፕላኑ ታስቦበት ሳይሆን በተፈጠረ ስህተት መመታቱን አስታውቃለች።

አውሮፕላኑ የኢራን ብሄራዊ አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ በሚገለገልበት “የተከለከለና ጥብቅ አካባቢ” በቅርብ ርቀት ማለፉን ተከትሎ በስህተት ተመቶ መውደቁን የሃገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

የኢራን ጦር ባወጣው መግለጫ “አውሮፕላኑ ተመቶ ለመውደቁ ኃላፊነት የሚወስዱ አካላት ተጠያቂ ይሆናሉም” ነው ያለው።

ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ የጠየቀው ጦሩ ወደፊት መሰል ስህተቶች እንዳይደገሙ ጥንቃቄ አደርጋለሁ ብሏል።

የኢራን ፕሬዚዳንት ሀሰን ሮሃኒ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት አደጋውን “ይቅር የማይባል ስህተት” ሲሉ ገልጸውታል።

በትናንትናው እለት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ “አውሮፕላኑ ተመቶ ሳይወድቅ እንዳልቀረ የሚያመላክቱ መረጃዎች” ደርሰውኛል ማለታቸው ይታወሳል።

ትራምፕ በበኩላቸው በአደጋው ላይ “ጥርጣሬ” አለኝ ማለታቸውም የሚታወስ ነው።

የደህንነት መረጃዎችን ዋቢ ያደረጉ በርካታ መገናኛ ብዙሃንም አውሮፕላኑ ከመውደቁ ቀደም ብሎ ሚሳኤል መተኮሱን የሚያመላክቱ የሳተላይት ምስሎች መገኘታቸውን ዘግበው ነበር።
ቴህራን በበኩሏ ውንጀላውን መሰረተ ቢስ ነው ስትል ቆይታለች።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.