Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሶማሊያ አልሸባብን ለማስወገድ በጋራ መስራታቸው የሀገራቱን ጠንካራ የትብብር መንፈስ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሶማሊያ የጋራ ጠላታቸውን አሸባሪው አልሸባብን ለማስወገድ በጋራ መስራታቸው ከምንጊዜውም በላይ የሀገራቱን ጠንካራ የትብብር መንፈስ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፥ አሸባሪው አልሸባብ በሶማሌ ክልል በኩል የሞከረውን ጥቃት ለመመከት እና የቡድኑ ታጣቂዎች የነበሩባቸውን ቦታዎች ለማስለቀቅ ሲደረግ የቆየው ዘመቻ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በአሁኑ ወቅት በጥቂት ቦታዎች ላይ የአሸባሪው አልሸባብ ታጣቂዎች እየተለቀሙ ነውም ብለዋል፡፡

በዋናነትም በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ፣ በህብረተሰቡ እንዲሁም በፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ትብብር ዘመቻው ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ትልቅ ውጤት ማምጣቱን ገልጸው፥ የጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የፌዴራል ሃይልም ሸሽተው ወደመጡበት ሲመለሱ የነበሩ የቡድኑ አባላት ወደግዛቱ እንዳይገቡ በርካታ ስራዎችን ሰርቷልም ነው ያሉት፡፡

ይህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ስራዎች ትልቅ ውጤት ማምጣታቸው አንዱ ማሳያ እንደሆነ አንስተው ፤ ለተገኘው ስኬት ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሶማሊያ የጋራ ጠላታቸውን አሸባሪው አልሸባብን ለማስወገድ በጋራ መስራታቸው ከምንጊዜውም በላይ የሀገራቱን ጠንካራ የትብብር መንፈስ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.