Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን በተለያዩ ሀገራት የሚወክሉ አምባሳደሮች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያን በተለያዩ ሀገራት የሚወክሉ አምባሳደሮች በዛሬው ዕለት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዋናው መስሪያ ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች እና ቆንስል ጀኔራሎች ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲያካሂዱት የነበረውን ዓመታዊ ስብሰባ ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው።

ተሳታፊዎቹ በዛሬው ዕለትም በታላቁ የህዳሴ ግድብ በመገኘት ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ ተመልክተዋል።

የግድቡ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ለአምሳደሮች የግድቡን አጠቃላይ የግንባታ ሂደት ገለፃ አድርገውላቸዋል።

በዚህ ወቅትም የኮርቻ ቅርጽ ያለውን የግድቡ ክፍል እንዲሁም ዋናውን የግድቡን ስፍራ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የነበሩት እና በአሁን ወቅት በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ግድቡ በዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ በማየታቸው ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ እፅቀስላሴ በበኩላቸው በጉብኝቱ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለፅ የህዳሴ ግድብ የኢትጵያውያን የአንድነት እና የላብ ዋጋ ነው ብለዋል።

ሌሎች አምባሳደሮችም የህዳሴ ግድብ በውጭ ሀገራት ሆነው ሲያዋጡ ለነበሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.