Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን በከፍተኛ ጭቆና ሲመራ የቆየው ህወሓት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ እያደረገ ነው-አትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 26፣ 2013 ( ኤፍ ቢ ሲ) ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን በከፍተኛ ጭቆና ሲመራ የቆየው ህወሓት አሁን ላይ ለትግራይ ክልል የሚደረጉ የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎችን በማደናቀፍ ድጋፍ እንዳይደርስ እያደረገ ነው” ሲሉ የአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል ምክትል ዳይሬክትር ብሮንዊን ብሩተን ገለጹ።
 
ብሮንዊን ብሩተን ሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታዎችን በተመለከተ ከቢቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ “በክልሉ አሁን ላይ የሰብአዊ ድጋፍ መስተጓጎል እንዲገጥም ያደረገው አሸባሪው ህወሓት ነው” ብለዋል።
 
የኢትዮጵያ መንግስት ያወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም ባለመቀበል አሸባሪው ድርጅት ውጊያ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀው÷ለትግራይ ክልል የሚደረገውን የሰብዓዊ ድጋፍ እያደናቀፈ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
 
ምክትል ዳይሬክተሯ አክለውም “አጎራባች አማራና አፋር ክልሎች ላይ ድርጅቱ ባደረገው ጥቃት ዜጎች ተፈናቅለዋል” ብለዋል።
 
በሌላ በኩል ሽብርተኛው ህወሃት ላለፉት 30 አመታት ገደማ አገሪቷን በአምባገነንነት መግዛቱን ገልጸው፤ የለውጡ ሂደት ከመጣ በኋላ ህወሃት የትግራይ ክልል በማስተዳደር የጦርነት ቅስቀሳ ሲያደርግ ቆይቶ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አብራርተዋል።
 
በተጨማሪም ሽብርተኛው ቡድን ጥቃቱን በማጠናከር በድጋሚ ወደ ስልጣን ለመምጣት ጦርነት መጀመሩን አመልክተው የፌደራል መንግስትም ይህንን ተከትሎ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ መግባቱን መግለፃቸውን ቢቢሲን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
በአሸባሪው ቡድን አገዛዝ ምክንያት ከሁለት አስርታት በላይ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ጭቆና፣ በፍርሃትና በማንነታቸው ጥቃት ውስጥ እንደነበሩ ምክትል ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.