Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን በ10 ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ታላላቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች ተጀምረዋል ‐ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያን በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በአፍሪካ ታላላቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል  አንዷ ማድረግን ዓላማ ያደረገ  ሰፋፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራን መንግስት መጀመሩን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 ኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን አስመልክቶ ትናንት በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት የተሰናዳ የደስታ መግለጫ ፕሮግራም ላይ በድንገት በመገኘት ንግግር አድረገዋል።

ዳያስፖራው ዝግጅት አለው ስባል ሰላምታ ለማቅረብ ነው የመጣሁት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥በጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚለዩበት አንድ መለያ በሰላም መኖር፣ የአገሪቱን ህግ ማክበር፣ ስራ መውደድ፣ እርስ በእርስ መግባባት፣ የተቸገረን የመርዳት ባህላቸው መሆኑን በማንሳት ሁሌም የሚመሰገኑበትን ይሄንን መልካም ስም እንዲጠብቁ መክረዋል።

ጅቡቲ ሁለተኛ ቤታችን ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ጅቡቲያውያኑ እኛን ይወዳሉ፤ እኛም ደግሞ አብዝተን እነሱን እንወዳቸዋለን ብለዋል፡፡

ዶ/ር አብይ መደመር በጅቡቲ እና በኢትዮጵያ በግልጽ መታዩትን ጠቅሰው ይሄንን በሁለቱ አገራት መካከል ያለ ጥብቅ ወዳጅነት የምታጠናክሩ ድልድዮች ጀግና ኢትዮጵያውያን ስለሆናችሁ በታማኝነት፣ በጨዋነትና በፍቅር እዚህ ካለው ህዝብ ጋር በመኖር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር እያንዳንዱ ዜጋ እንደ አምባሳደር እንዲሰራ አደራ እላለሁም ነው ያሉት።

ስለ ኖቤል ሽልማቱ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኖቤል ሽልማቱ በአንድ ሰው ስም መነገር ስላለበት እንጂ ሽልማቱ የሁላችሁም ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰፋፊ ስራዎች መጀመሩን፣ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላላቅ ኢኮኖሚ አንዷ እንድትሆን እየሰራ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን እና የኤርትራ ብልጽግና መሆኑን በመግለፅ፥ በውስጣችንም በአጎራባች አገራት ሰላም እንዲኖር እንሰራለን ብለዋል።

በሚቀጥለው ምርጫ ከተመረጥን እንሰራለን ካልተመረጥን አቅፈን በማስረከብ አርዓያ የሆነ ስራ እንሰራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ወቅት ተሸንፎ ስልጣንን በስርዓት ማስረከብ ከዚህ ኖቤል የሚበልጥ እንጂ የሚተናነስ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ስደት እንዲያበቃ ለልጆቻችን የምትበጅ ኢትዮጵያን ሰርተን ማቆየት አለብን በማለት ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡

በጅቡቲ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉስልጣን አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሐመድ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ መገኘት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በጅቡቲ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስም ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከኤምባሲው ያገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.