Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን ከኤርትራ የአሰብ ወደብ ጋር የሚያስተሳስረው  የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ከኤርትራ የአሰብ ወደብ ጋር የሚያስተሳስረው የሜሎዶኒ መገንጠያ – ማንዳ – ቡሬ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሊገነባ ነው።

በነገው ዕለትም ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ፕሮጀክቱን በይፋ የማስጀመር መርሃ ግብር ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዕለቱ በሚኖረው መርሃ -ግብርም ግንባታው የተጠናቀቀው የዲቾቶ – ጋላፊ የሲሚንቶ ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትም ይመረቃል።

የሜሎዶኒ መገንጠያ – ማንዳ – ቡሬ  መንገድ ሲጠናቀቅ   ወደ አሰብ ወደብ የሚዘልቅ መንገድ እንደመሆኑ ለኢትዮጵያ የተሻለ የወጪ ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ መሳለጥ አይነተኛ ሚናውን ይጫወታል፡፡

71 ነጥብ 65 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ይህን ፕሮጀክት 2 ቢሊየን 85 ሚሊየን 985 ሺህ ብር በሆነ ወጪ ጨረታውን አሸንፎ ግንባታውን የሚያከናውነው ሻንዶንግ ሊኪኖ ግሩፕ የተባለ የወጭ የስራ ተቋራጭ ድርጅት ነው።

የግንባታውን የማማከርና የቁጥጥር ስራ ደግሞ ስሜክ ኢንተርናሽናል እንዲሁም ቫሊዩ ኢንጅነሪንግ በንዑስ ተቋራጭነት ይሳተፋል ።

ለፕሮጀክቱ ግንባታ ማስፈጸሚያ  ወጪም የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት ነው፡፡

በአገልግሎት ሳቢያ የተጎዳ የአስፋልት መንገድና ከ6 ሜትር ያልበለጠስፋት የነበረውን በቀጣይ ከተሞች ላይ 19 ሜትር እንዲሁም በገጠር ደግሞ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 1ዐ ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የሚገነባ ይሆናል።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለአመታት ተቋርጦ የነበረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዳግም በመጀመሩ መስመሩን ለሚጠቀሙ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

በተያያዘ ዜናም 78 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የዲቾቶ – ጋላፊ መገንጠያ – ኤሊዳር – በልሆ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን ፕሮጀክት በነገው ዕለትም በይፋ ይመረቃል።

መንገዱን ለመገንባት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታ ያካሄደው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የተባለ የመንግስት ልማት ድርጅት ነው።

የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ኢንጂነር ዘውዴ እስክንድርና ከሲም አማካሪ መሃንዲስ በጥምረት ተሳትፈውበታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም የመንገድ ግንባታውን ለማካሄድ የዋለውን ወጪ ሙሉ በሙሉ እንደሸፈነው ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አካባቢው ባለው ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ ግንባታው በሲሚንቶ ኮንክሪት ደረጃ የተገነባ ሲሆን   ይህም የአየር ጸባዩን የመቋቋም እና የግልጋሎት ዘመኑ እንዲጨምር ያደርጋል ።

የዲቾቶ – ጋላፊ መገንጠያ – ኤሊዳር – በልሆ መንገድ መገንባት አዲሱን የታጁራ ወደብ በአማራጭነት  ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር በነባሩ ጅቡቲ ወደብ ይፈጠር የነበረውን የትራንስፖርት ጫና እና መጨናነቅ እንደሚያቃልለው ይጠበቃል።

ፕሮጀክቱ የሀገሪቷ የወጪ ገቢ ንግድ የሚካሄድበት ኮሪደር እንደመሆኑ መስመሩን የሚጠቀሙ ብዙ ቁጥር ያላቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች ክብደት የመሸከም አቅም እንዲኖራቸው ታሳቢ ያደረገ ነው ፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.