Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያዊያን ለከፋፋይ ሃሳቦች ጆሮ ሳይሰጡ ለአገር ሠላምና አንድነት ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያዊያን ለከፋፋይ ሃሳቦች ጆሯቸውን ሳይሰጡ ለአገር ሠላምና አንድነት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ የአድዋ ድል በዓል ታዳሚዎች ጥሪ አቀረቡ።

125ኛው የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ በደማቅ ሥነ ስርዓት ተከብሯል።

በምኒልክ አደባባይ የነበረው የበዓል አከባበር ሲጠናቀቅ በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎችና ወጣቶች የአድዋ ዘመቻ መነሻ ወደሆነው አድዋ ድልድይ በእግር ጉዞ አቅንተዋል።

በጉዟቸውም በጎዳናዎች ላይ ጋሻና ጦር ይዘው፣ በፈረስ ተቀምጠው ፉከራ፣ ቀረርቶና ሽለላ በማሳየት በዓሉን አድምቀውታል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ዜጎች በተለይ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ከሚሰራጩ አፍራሽና ከፋፋይ ሃሳቦች ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

አባቶች በአንድነት በመሆን ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የሚተርፈውን የአድዋ ድል ማስመዝገባቸውን በመግለፅ፤  የአንድነትን ውጤት ከጀግኖች አባቶችና እናቶች ተግባር መማር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ወጣት ናትናኤል ወንድምአገኝ “አባቶች በአድዋ ጦርነት ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው አገር አቆይተውልናል፤ አሁንም ዳር ድንበሯን ለመድፈር ለሚመኙ በአንድነት በመቆም ልንመክት ይገባል” ብሏል።

ወጣት ህሊና መንበሩ ደግሞ “ከአድዋ ፍቅርን፣ አንድነትን እንማራለን፣ አሁን ያለው ትውልድ በዘር መከፋፈል የለበትም” የሚል ሀሳብ አንስታለች።

“የኢትዮጵያ አንድነት አይሸረሸርም፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች” ያለው ደግሞ ወጣት ተመስገን ኪዳኔ ነው።

ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ወጣት ልዑልሰገድ ወርቁ  በበኩሉ ሠላም ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ገልጾ ÷ የአገርን ሠላም ለማምጣት እያንዳንዱ ሰው ከራሱ መጀመር እንዳለበት አመልክቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.