Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለማጽናት በጋራ የከፈሉትን መስዋዕትነት ትውልዱ መዘንጋት የለበትም – የታሪክና ባሕል ተመራማሪዎች

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 27፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀደምት እናትና አባት ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለማጽናት በጋራ የከፈሉትን መስዋዕትነት ትውልዱ መዘንጋት የለበትም ሲሉ የታሪክና ባሕል ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራኑ፥ ሀገርን በአንድነት ለማስቀጠል የታለፉ የታሪክ ምዕራፎችን ልንማርባቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ተመራማሪው አቶ ተረፈ ወርቁ÷ አሁን የተዘነጋ የሚመስለው ኢትዮጵያዊ ማንነት ከሀገር አልፎ ለሌሎች ሀገራትም መትረፍ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በጠንካራ የትብብር መንፈስ ቀደምት አባትና እናቶች ታሪክ ሰርተው ማለፋቸውን ያነሱት ተመራማሪው ፥ ልዩነቶችን ለማስተናገድ ሲጠቀሙት የቆየው ብስለት እና አስተዋይነት የተሞላበትን ስልት አሁን ላይ ልንማርበት ይገባል ብለዋል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ሶሻል አንትሮፖሎጅ መምህርና ተመራማሪ ተመስገን ለሜሳ በበኩላቸው÷ የሃሳብ ልዩነቶች በታሪክ ሕዝብን ከሕዝብ የለዩ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡

ለሀገር የተከፈለ መስዋዕትነትን በቅጡ ያለመረዳት፣ የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፣ ብዝሃነት እንዳይስተናገድ ግርዶሽን የፈጠሩ የጥላቻ ስብከቶች አሉታዊ ውጤታቸው እየታየ መሆኑንም ነው ምሁራኑ የገለጹት፡፡

መሰል ችግሮችን ማረቅ እንደሚገባ የገለጹት ምሁራኑ÷ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም ዜጎች ቆም ብለው ሊያስተውሉ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

በአወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.