Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን የአንድነት እና መከባበር እሴቶቻቸውን ሊያስጠብቁ ይገባል- የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ቀደም የነበሩትን የአንድነት እና መከባበር እሴቶች ሊያስጠብቁ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አሁን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችም በፍጥነት እንዲቆሙ መንግስት ህግ የማስከበር ስራ ሊሰራ እንደሚገባም አስተያየት ሰጭዎቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ለተከሰቱት ግጭቶች እና ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለህግ መቅረብ አለባቸው ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ አጥፊዎቹን በማጋለጥ ላይም ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባልም ብለዋል።

አቶ አህመድ ሁሴን የተባሉ አስተያየት ሰጪ ሰላም ከቃላት በላይ ነው ያሉ ሲሆን እንኳንስ ኢትዮጵያን ሰላም ማድረግ ቀርቶ ለሌሎችም ሀገሮች ሰላም ለመሆን ሰርተናል በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ ምሳሌ አድርገው ይናገራሉ።

ሰላም ሲኖር ስለነገ ማሰብ ይቻላል ፤ ሰው ተስፋ ይኖረዋል ፤ ህፃናትም ሀገራቸውን የመረከብ ህልማቸው እውን ይሆናል ብለዋል አስተያየት ሰጪዎች፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የሰላም ሁኔታ እንደሚያሰጋቸው የገለፁት ነዋሪዎች ሰሞኑን የተፈጠረው አለመረጋጋት መመከት ካልተቻለ ኢትዮጵያን እንደ ሌሎች ሰላም ያጡ ሀገራት ቀውስ ውስጥ ሊከት የሚችል ነው ብለዋል፡፡

አስተያየት ሰጭዎቹ በኢትዮጵያ የሀይማኖትም ሆነ የብሄር ልዩነቶች ብዙም አይታዩም ያሉ ሲሆን የአንድ ሀይማኖት ተከታይ ለሌላው ሀይማኖት ያለውን ክብር እና እርስ በርሰ የመተባበር ሁኔታም በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

ይህን አብሮነት እና መከባበርም ህብረተሰቡ ማስቀጠል እንደሚገባ በማንሳት አሁን የተፈጠሩትን ግጭቶች ብሄር እና ሀይማኖት ተኮር ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት ሀገርን የመበተን አላማ ያላቸው ናቸው ብለዋል።

በሀገሪቱ የተፈፀረው ችግር ለመቅረፍ ለሰላም ዘብ መቆም እና ችግር ፈጣሪ የሆኑ ኣካላትን ለህግ እንዲቀርቡ የማጋለጥ ስራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

መንግስም የህብረተሰቡን የመኖር ህልውና እንዲጠብቅ እና የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ጠይቀዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.