Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ለህዝባቸው ሰላም፣ ትብብር፣ አብሮ መኖርና ልማት ሊሰሩ የሚገባቸው ጊዜ አሁን ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ለህዝባቸው ሰላም፣ ትብብር፣ አብሮ መኖርና ልማት ሊሰሩ የሚገባቸው ጊዜ አሁን መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ባወጡት መግለጫ፥ ኢትዮጵያ በግብርና፣ የማምረቻ እና በሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ መሰረት ያደረገ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራች መሆኗን አንስተዋል።
አክለውም የማህብራዊ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ለዜጎቿ ጥራቱን የጠበቀ የጤና እና የትምህርት አገልግሎት እንዲሁም የንፁህ መጠጥ ውሃ እቅርቦትን ለማሻሻል እየሰራች ነው ብለዋል።
ይህንን በማሳካቱ ሂደት ውስጥም ሀገሪቱ ለታዳሽ ሀይል ምንጭ ልዩ ትኩረት መስጠቷንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱት።
የኤሌክትሪከ ሀይል በኢትዮጵያ በእጅጉ እጥረት ያለበት አገልግለሎት መሆኑን በማነሳት 53 በመቶ ኢትዮጵያውያን ማለትም 60 ሚሊየን ህዝብ በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሀይል እንደማያገኝ ገልፀዋል።
ያለ ኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት የትኛውም ሀገር ድህነትን ድል ነስቶ ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ የሚያድርግ እድገትን በማረጋገጥ ዜጎቹ ክብር ያለው ህይወት እንዲመሩ ማድረግ እንደማይችል አስገንዝበዋል። በዚህም ሂደት ዘላቂ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና የአካባቢ ልማት ማምጣት ይቻላል ነው ያሉት።

በመሆኑም 85 ከመቶ የሚሆነው የናይል  ወንዝ ድረሻ ከኢትዮጵያ ተራራዎች የሚመነጭ እንደመሆኑ፥  አገራችን ያለባትን መሠረታዊ የኤሌክትሪክ ሃይል ችግር ለመፍታት  በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት አማካይነት ሃይል በማመንጨት ሶስቱንም አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባር ማከናወኗ ተገቢ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የናይል ወንዝን የጎላ ጉዳት ሳያደርስ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መልማት እና የተፋሰሱን ሀገራት ህዝቦች መጥቀም እንደሚችል ኢትዮጵያ ታምናለች ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም የዚህን የትብብር መርህ ማሳያ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት እየተገነባ ያለው ግድቡ ለሱዳንና ግብፅ ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ አካባቢ በርካታ ጥቅሞችን እንደያዘ አስረድዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አገልግሎቱ ወጥ በሆነ መልኩ ዓመቱን ሙሉ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ይህም ማለት ግድቡ ምንም ዓይነት ውሃ እንደማይጠቀምና ይልቁንም ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ያልተቋረጠ ውሃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመግለጫቸው ብዙ ያልተነገረላቸው ያሏቸውን ሱዳንና ግብፅ ከግድቡ ሊያገኙት የሚችሉትን በርካታ ጠቀሜታዎችንም ዘርዝረዋል።
ለአብነትም ሀይል አመንጭቶ በቋሚነትውሃ የሚለቀው ግድቡ ለሱዳን ህዝብ፣ ግብርና ለተፋሰሱ በአጠቃላይ አስተማማኝ ውሃ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
ግብፅም ብትሆን በየዓመቱ በትነት እና በጎርፍ የሚባክንባትን በቢሊየን ኩዪቢክ የሚገመት ውሃ የሚቆጥብላት ግድብ ነው ብለዋል።
እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በሚደረጉ ንግግሮች የግድቡ አሉታዊ ተፅእኖዎች ተብለው የሚነሱት ጎልተው ወጥተው ግድቡ ሊያመጣ የሚችለውን የትብብር መንፈስ እና በርካታ ችግሮችን መፍታቱን የተመለከቱት ደብዝዘዋል።
ሆኖም ግድቡ ለሀገራቱ ህዝቦች ሰላማዊነት፣ ትብብር፣ አብሮ መኖርና የመልማት እድልን ይዞ የመጣ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
የናይል ወንዝ በአጠቃላይ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በተለይ ለሶስቱ ሀገራት የሰላም፣ የትብብርና የልማት ዓላማ መሳካት ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.