Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የትኛውንም መሥዋዕትነት ትከፍላለች- መንግስት

ሰበር ዜና
 
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የትኛውንም መሥዋዕትነት ትከፍላለች ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
 
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል፡፡
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል÷
 
 
ኢትዮጵያ ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የትኛውንም መሥዋዕትነት ትከፍላለች!
የኢትዮጵያ ችግሮችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ መፍታት እንደሚገባ መንግሥት በጽኑ ያምናል። ይሄንንም ከለውጡ መጀመሪያ ጀምሮ በግልጽ ሲገልጥ ቆይቷል፡፡ አንድን ሕመም ለማዳን እንደሚወሰዱ የተለያዩ መድኃኒቶች፣ አንድን ሀገራዊ ችግርም በሁሉም የመፍትሔ መንገዶች እንዳይመለሱ አድርጎ መፍታት ይገባል። ኢትዮጵያ ከየአቅጣጫው የተከፈቱባትን ጥቃት በጀግኖች ልጆቿ እየመከተች ነው።
 
በዓለም አቀፍ መድረክ ሊገዳደሩን ያሰቡትን በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ድምጽና ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ረትተናል። ዘመን ተሻጋሪ ፖለቲካዊ ችግሮችን በአካታች ሀገራዊ ምክክር ለመፍታት እንዲቻል መንግሥት ገለልተኛ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚጠበቅበትን እየተወጣ ይገኛል። በሁሉም መስክ ኢትዮጵያ እያሸነፈች የለውጥ ጉዞዋን እንደቀጠለች ነው፡፡
 
በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠ መንግሥት፣ አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ከሚጠበቅበት ሞራላዊ ግዴታዎች አንዱ ምሕረት በመሆኑ ለተሻለ ፖለቲካዊ ምኅዳር ሲባል የተወሰኑ እሥረኞችን መንግሥት ዛሬ በምሕረት ከእሥር ፈትቷል። ይህ ምሕረት ከዚህ በፊት በተፈጸመ ጥፋት የታሠሩትንም ሆነ በቅርቡ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሠሩትን ይጨምራል። መንግሥት ይሄንን ውሳኔ ሲወስን ዓላማው የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልክና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በሀገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ ለመክፈት ነው። በተጨማሪም የሕዝብን ጥያቄዎች ከግምት በማስገባትና ምንጊዜም ለሰላማዊ ፖለቲካ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ነው።
 
የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና ለአካታች ሀገራዊ ምክክር ሲል መንግሥት በምሕረት የፈታቸው አካላትም፣ ካለፈው የጥፋት መንገድ ተምረው፣ የተሻለ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አስተዋጽዖ በማድረግ፣ ሀገራቸውንና ሕዝባቸዉን ይክሳሉ ብሎ መንግሥት ያምናል። ከግጭትና ከከፋፋይ መንገዶች ይልቅ ለሰላማዊ ፖለቲካ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉም መንግሥት ተስፋ ያደርጋል።
 
መንግሥት ይሄንን ውሳኔ በአንድ በኩል ሲወስን በሌላ በኩል ደግሞ ያለፉ ዋጋ አስከፋይና ግጭት ጠማቂ አካሄዶች በጭራሽ እንዲደገሙ አይፈቅድም። ፍትሕና ምሕረትም በየሚዛናቸው እንዲጓዙ መንግሥት ይፈልጋል። በሂደቱ የተጎዱ ወገኖች እንደሚኖሩ መንግሥት ያምናል። የእነዚህ ተጎጂ ዜጎች ቁስል በሽግግር ፍትሕ የሚካስ ይሆናል። እነዚህ ተጎጂ ዜጎች ሕመማቸው ለኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ ሸክማቸውን መንግሥትና ሕዝብ በጋራ እንሸከምላቸዋለን። ከእሥር የተፈቱ ወገኖችም ጭምር የተጎጂዎችን ሸክም የመሸከም ዕዳ አለባቸው።
መንግሥት ይሄንን ውሳኔ የወሰነው በዋናነት ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ነው። ኢትዮጵያ የመሐሪነቷን ዋጋ እንድታገኝ፣ የኢትዮጵያን ምሕረት ያገኙት አካላት፣ ምሕረቱን ያገኙበትን ዋጋ ይረዱታል ብሎ መንግሥት ያምናል። የኢትዮጵያ ነባር ችግሮች የሚፈቱት በሰላማዊ ፖለቲካዊ ተዋሥኦ፣ በሆደ ሰፊነትና አዎንታዊ ሚናን በመጫወት ነው።
 
ለዚህ ደግሞ መንግሥት ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ቅድምናውን ይወስዳል። ዛሬም ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም ሲል መንግሥት የተወሰኑ እሥረኞችን በምሕረት ፈትቷል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.