Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በልጆቿ የመተባበርና የመተሳሰብ ባህል ሊገጥማት የሚችለውን የምጣኔ ኃብት ማሽቆልቆል መቋቋም ትችላለች – የምጣኔ ኃብት ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 8 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በልጆቿ የመተባበርና የመተሳሰብ ባህል ሊገጥማት የሚችለውን የምጣኔ ኃብት ማሽቆልቆል መቋቋም እንደምትችል በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ኃብት ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከጦርነቱ በኋላ ሊገጥማት የሚችለውን የኢኮኖሚ ድቀት ለማካካስ ከወትሮው በተለየ ግብርናን በማጠናከር ምርታማነትን ማሳደግ ይገባታል።

ጦርነት የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ያልተጠበቀ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት በማድረግ፣ የአምራች ኃይልን ከሥራ መስክ በማፈናቀልና ሌሎችም ተጓዳኝ ችግሮችን በማስከተል እንደሚጎዳ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ኃብት ትምህርት ክፍል መምህር ወንድምሁነኝ አጥላው እንዳሉት፥ አሁን እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ሀገርን ለማዳን ከተደረገው ዘመቻ ጋር በተወሰነ መልኩ ተያያዥነት አለው።

“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቶሎ እንዲያገግም ከሚያስችሉ መልካም ሁኔታዎች መከካከል የህዝቡ አንድነትና ከጥንት ጀምሮ የመጣው የመተሳሰብና መደጋገፍ ባህል አንዱ ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል ከሰሜኑ የሀገራችን ከፍል ውጭ ባሉት አካባቢዎች ማካካስን መሠረት ያደረገ የግብርና ሥራ እየተሰራ መሆኑን እንደ ጥሩ የመፍትሄ መንገድ ጠቅሰዋል።

ሌላው የምጣኔ ኃብት መምህር ጋሻው ፍስሐ በሰጡት አስተያየት በጦርነት ምክንያት ያልተገባ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በመጣልና የገበያ አሻጥር በመፍጠር እጅ ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ አንዳንድ ራስ ወዳድ ምዕራባውያን ሀገሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

ለዚህም የአጎዋን እገዳ የጠቀሱ ሲሆን በጦርነቱ ወገንተኛ በመሆን አሸባሪው በርትቶ ኢትዮጵያ ግን ኢኮኖሚዋ እንዲቀጭጭ ተፈልጎ የተሰራ ሴራ መሆኑን በአብነት ጠቅሰዋል።

የሽብር ቡድኑን በመደገፍ በኢትዮጵያ ጦርነት እንዲካሄድ ያደረጉት ጋላቢዎቹ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገሮች ጦርነቱን እንደ ምክንያት በመጠቀም የኢኮኖሚ ቅጣት ለማስከተል እንደሆነ ተረድቶ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ ራስን መቻል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ከዚሁ ችግር ጋር በተያያዘ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት እንዲረግብ ለግብርና የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

እንደ ቀድሞው ዝናብ ጠብቆ ብቻ ከማረስ ባህል በመውጣት መስኖ በመጠቀም በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት አንዱ የኢኮኖሚ ማገገሚያ ስልት መሆኑንም ገልጸዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.