Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በቴል አቪቭ በተካሄደ የቱሪዝም ዐውደ ርዕይና ኮንፈረንስ ላይ ተሳተፈች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በእስራኤል ቴል አቪቭ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ዐውደ ርዕይና ኮንፈረንስ ላይ ተሳተፈች።

የቱሪዝም ዐውደ ርዕይና ኮንፈረንሱ “ዓለም አቀፍ የሜዲትራኒያን የቱሪዝም ገበያ 2020” በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 3 እስከ የካቲት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ መካሄዱን በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መላከው መረጃ አመላክቷል።

ዐውደ ርዕይና ኮንፈረንሱ ላይ ስለ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት ለተሳታፊዎች ገለጻ ተደርጓል።

በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠባባቂ ጉዳይ ፈጻሚ አቶ ልዑልሰገድ ታደሰ፥ ኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶችን፣ የታሪክ ሃብት እና የማራኪ ብዝሀነቷ ነጸብራቅ የሆኑ ዘጠኝ የዓለም ድንቅየ ስፍራዎችን እና አራት የማይዳሰሱ ቅርሶችን የያዘች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

አያይዘውም እስራኤላውያን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ኤምባሲው ኢትዮጵያን መጎብኘት ለሚፈልጉ እስራኤላውያን፣ አስጎብኚዎች እና ጸሃፊዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፥ መንግስት ለመስኩ የሰጠውን ትኩረት በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው በቱሪዝም ኢትዮጵያ የተለዩ አምስቱ የኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለተሳታፊዎቹ አብራርተውላቸዋል።

ከዐውደ ርዕዩና ኮንፈረንሱ ጎን ለጎን የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ግርማ በቴል አቪቭ ከተማ አስተዳደር ተገኝተው ከከተማዋ የውጭ ግንኙነት ክፍል ዳይሬክተር ኤሊያቭ ብሊዞውስኪ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም በእስራኤል የኢትዮጵያን ቱሪዝም የሚያስተዋውቅ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.