Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በ”ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ” እንዲሁም በ”አጎዋ” ላይ ያላትን አቋም ለአሜሪካው ምክር ቤት አባል አስረዳች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ስለሺ በቀለ በአሜሪካ ምክር ቤት የቀረበው የኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ላይ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት መታገዷን በተመለከተ መንግስት ያለውን አቋም ለአሜሪካው የምክር ቤት አባል ጆን ጋራሜንዲ አስረድተዋል።

አምባሳደሩ ከአሜሪካው የምክር ቤት አባል ጆን ጋራሜንዲ ጋር ፍሬያማና ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

አምባሳደር ስለሺ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉትን የልማት ሥራዎች እና በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በቆየው ግጭት እና ግጭቱን ለመፍታት በተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ ማብራሪያ መሥጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመላክቷል፡፡

አምባሳደር ስለሺም የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ጆን ጋራሜንዲ መርህ ላይ በተመሰረተ ዕይታ የኢትዮጵያን ጉዳይ በመመልከታቸው እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያላቸውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት፣ ትብብርና አጋርነታቸውንም ሀገራቱ ወደቀድሞ ሁኔታው መመለስ እንዳለባቸው አምባሳደር ስለሺ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በውይይታቸው የአሜሪካ የምክር ቤት አባል ጋራሜንዲ ከኢትዮጵያን ጎን እንደሚቆሙ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.