Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን መጠቀሟ ኢኮኖሚውን ከመደገፍ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው-ወ/ሮ ዳግማዊት

ኢትዮጵያ በጎረቤት አገራት ያሉ አማራጭ ወደቦችን የመጠቀም ዕድሎቿን ማስፋቷ ኢኮኖሚውን ከመደገፉም ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ  እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም ያሏትን እድሎች የማስፋት ተግባራት እያከናወነች ነው።

ኢትዮጵያ በወጪና ገቢ ንግድ ከጅቡቲ ወደብ በተጨማሪ የታጁራ፣ በርበራና ፖርት ሱዳን ወደቦችን እየተጠቀመች እንደምትገኝም ገልጸዋል።

እያደገ የመጣውን የገቢና ወጪ ንግድ መሸከም የሚያስችል ተጨማሪ ወደብ መጠቀም እንዳስፈለገ ጠቁመው፤ የላሙ ወደብን ለመጠቀም ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ እንደሆነ ተናግረዋል።

አገሪቱ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም በመቻሏ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን እንድታሰፋ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው፤ ወጪን በመቀነስም ለልማት ማዋል የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆኑን አብራርተዋል።

ለአብነትም በዚህ ዓመት በታጁራ ወደብ ብቻ ከ700 ሺህ ቶን በላይ የድንጋይ ከሰልና ከ200 ሺህ ቶን በላይ ካርጎ መግባት በመቻሉ በጅቡቲ ወደብ ላይ ይወሰድ የነበረውን ጊዜ እንዳሳጠረ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ወደብ ካላቸው አገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት አብሮ ለመልማትና የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ከወደብ አገልግሎቱ በተጨማሪ በመሰረተ ልማት ስራዎችም መንገዶች ወደሌሎች የቀጣናው አገሮች መሸጋገሪያ እንዲሆኑ በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ይበልጥ የሚጠናከርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከካይሮ እስከ ኬፕታውን የሚዘረጋው የመንገድ አካል የሆነው ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ መጠቆማቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.