Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ሕንድ ግንኙነታቸውን ለማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 27፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላም እና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ከሕንድ አምባሳደር ሮበርት ሸትኪንቶንግ እና ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤ ሁለቱ ሀገራት የፓርላማ የወዳጅነት ቡድኖቻቸውን በማጠናከር በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች የበለጠ ተቀራርበው መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በታሪክ እና በባሕል ተመሳሳይነት እንዳላቸው የገለጹት ዶክተር ነገሪ ከጥንት የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በኢፌዴሪ ፓርላማ በኩል ሁለንተናዊ ጥረት የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ኢንቨስት ከሚያደርጉ ሀገራት ከቻይና በመቀጠል ሕንድ በሁለተኛ ደረጃ እንደምትገኝም አስታውሰዋል፡፡

ሕንድ በአለም 5ኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆኗን በመጥቀስ፥ በዚሁ መሰረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጎልበት መሠራት ይኖርበታልም ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግስት ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን፥ በሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን የወደሙ መሠረተ-ልማቶችን የመጠገን ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ፥ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ወንጀለኞችን አድኖ ለህግ የማቅረብ ስራ በፌዴራል ፖሊስ እየተሰራ እንዳለም አስረድተዋል።

አምባሳደር ሮበርት በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ሕንድ ከጥንት ጀምሮ የነበራቸውን መልካም ግንኙነት እና የትብብር መንፈስ የበለጠ ለማሳደግ በትምህርት፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና በሌሎችም በጋራ ሊያሠሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ተባብረው እንዲሠሩ ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ፣ በባሕል በጋራ በመሥራት ያላቸውን ትብብር እንዲያሳድጉ ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላት ማስታወቃቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.