Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የ31 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የ31 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የዛሬ ሳምንት የአፍሪካ ልማት ፈንድ ድጋፉን ያጸደቀ ሲሆን፥ ይህን ተከትሎም በዛሬው እለት የፊርማ ስነ ስርአት ተካሂዷል፡፡

ስምምነቱን የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ያስሚን ዎሃብረቢ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አብዱ ካማራ መፈራረማቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያ የህጻናትን መቀንጨር ለመከላከልና የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ድጋፉ ከአምስት ዓመት በታች ለሆናቸው ህፃናት የሚቀርበውን ዘርፈ ብዙ የተመጣጠነ ምግብ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ፈንዱ አስታውቋል።

ጤናን ለማሻሻል ፣ የተለያዩ የተመጣጠኑ የምግብ አይነቶችን ለማቅረብ፣ በህጻናት አመጋገብ ዙሪያ እውቀት እና አመለካከትን ለማሻሻል እንዲሁም ጡት ማጥባትን ፣ እንክብካቤን እና ንፅህናን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ባንኩ ገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ፕሮግራሙን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ለመተግበር የመሰረተ ልማትን ዝርጋታንም ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚገኙ 40 ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑም ተጠቁሟል።

ይህ ፕሮጀክት የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦቱን ውጤታማ ለማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረገ መሰረተ ልማትን መገንባት ፣ የቤተሰብ ድጋፍ ፣ የተመጣጠነ ምግብ ምርትን ማስተዋወቅ እንዲሁም ተቋማዊ ስርዓትን ማጠናከር እና አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.