Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች ነው -የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች ጉዳይ ዳይሬክተር ኤልያስ መላኩ እንደገለጹት ÷ኢትዮጵያ ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ለአህጉሪቷ አገሮች የእርስ በርስ ትብብር የበኩሏን ሚና እየተወጣች ነው፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት የዚሁ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በናይጄሪያ ያደረጉት ጉብኝትን ተከትሎ የሁለቱ አገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ተገናኝተው የአገራቱን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን ስለማድረጋቸው አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይም ከሴኔጋል፣ አይቬሪኮስት፣ ቶጎና ሌሎችም ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ጠንካራ አህጉር ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት ሰፊ የበረራ ሽፋን እንዳለው ጠቅሰው÷ ይህም ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር ያግዛል ነው ያሉት፡፡

መሰል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት ዳይሬክተሩ÷በአገራቱ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን አማካኝነት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጠንካራ ትስስር እየፈጠረች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ሥራ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማስፋት በቁርጠኝነት እንደምትሰራም ተናግረዋል፡፡

ይህም አህጉሪቷን ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ሚናው የጎላ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.