Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከግለሰቦችና ድርጅቶች በላይ ናት – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከግለሰቦችና ድርጅቶች በላይ ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ገለፁ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች

ክቡራትና ክቡራን

ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት። ሐሳባችን፣ ሥራችንና ንግግራችን ሁሉ ታላቅነቷን የሚመጥን መሆን ቢችል መልካም ነው። ካልሆነ በኢትዮጵያ ሚዛን ተመዝነን እንቀልላለን።
ኢትዮጵያ መዝና ታላቅነቱን የመሰከረችለትን ማንም አያቀልለውም። ኢትዮጵያ ያቀለለችውንም ማንም አያከብደውም። ታሪካችን ይሄንን ይመሰክራል፤ ዛሬም እየመሰከረ ነው።
ኢትዮጵያ ታላቅ ናት ስንል ከዜጎቿም፣ ከመሪዎቿም፤ ታላቅ ገድል ፈጽመናል ከሚሉ ሰዎች ሁሉ በላይ ታላቅ ናት ማለታችን ነው። በየትኛውም ዘርፍ ያሉ ልሂቃን፣ የትኛውንም የተቀደሰ አጀንዳ አንግበው የተመሠረቱ ድርጅቶች፣ ሐሳብና ርዕዮተ ዓለሞች ሁሉም ከኢትዮጵያ በታች ናቸው።

ኢትዮጵያ በሺዎች ዘመናት ሠርተውና ተጋድለው ያለፉ መሪዎችና ዜጎች ድምር ውጤት ናት።

ኢትዮጵያ – ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ሰፍተውና መልተው የሚኖሩ፣ የሚሠሩና የሚጋደሉ ልዩ ልዩ ሕዝቦች ውጤት ናት። ታሪክ ያልመዘገባቸው፣ የታሪክ ድርሳናት የማያውቋቸው እልፍ አእላፍ ታሪክ ሠሪዎች በደምና በአጥንት፣ በላብና በወዝ በጽኑዕ መሠረት ላይ የገነቧት ሀገር ናት።

ግለሰቦች ለኢትዮጵያ የማይናቅ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ፤ የኢትዮጵያ ህልውና ግን በግለሰቦች አይወሰንም። ግለሰቦች ለክብሯ ሲሉ ደማቸውን ሊያፈስሱ፣ አጥንታቸውን ሊከሰክሱ፣ መስዕዋት ሆነው ሊያስቀጥሏት ይወስኑ ይሆናል፤ ነገር ግን “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው የቤት እንስሳ፥ ለግለሰቦች ሲባል ሀገር እንድትሞት ወይም እንድትኖር ለድርድር አትቀርብም።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ታላላቅ ጀግኖች ነበሯት። በየጦር ሜዳው ታላላቅ ጀብዱ የፈጸሙ አርበኞች፣ በየእውቀት መስኩ አርቀውና አስፍተው የተመለከቱ አሰላሳዮች፣ በየውድድር ሜዳው አይበገሬነታቸውን ያስመሰከሩ ተፋላሚዎች፣ በሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አንቱታን ያተረፉ መሪዎች ከማህጸኗ በቅለዋል፤ ወደፊትም ይበቅላሉ። ኢትዮጵያ እኛን እንጂ፣ እኛ ኢትዮጵያን አልፈጠርናትም።

እኛ ከመፈጠራችን በፊት ኖራለች፤ ከእኛ መሐል አንዳችን ስለጎደልን አትጠፋም። እኛ በዘመናት መካከል ከመጡ አርበኞች፣ አሰላሳዮች፣ ተፋላሚዎችና መሪዎች እንደ አንዱ ነን። በተሰጠን እድሜ የየበኩላችንን ጡብ አስቀምጠን እንሄዳለን።

መጭውም የአቅሙን አክሎበት ይቀጥላል። በየትውልዱ አያሌ ዜጎችን እያፈራች መገስገሷን ትቀጥላለች። የትውልድ ቅብብሎሽ ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” እያደረጋት ወደፊት ትጓዛለች።
የእኛ ሚና ቀደምቶቻችን የጀመሩትን መልካም ተግባር አጎልብተንና አሳምረን ለመጪው ትውልድ ማቀበል ነው። ከእኛ በኋላ የሚመጣውም ቅብብሎሹን ቀጥሎ፣ እኛ የጀመርነውን እያጎለበተ ያስቀጥላል።

የሕዳሴ ግድብን ብንወስድ ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸው ወሳኝ ፕሮጀክት አንዱ ነው።

ያስጀመሩት መሪዎች ቢያልፉም ሕዝብና መንግሥት እየገነቡት ይገኛል። ሌሎችም የተጀመሩ የመንገድ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የመስኖ ግድብ፣ የኃይል ፕሮጀክቶችን ሕዝብና መንግሥት ካለፉት ተረክቦ አስቀጥሏቸዋል። ማን ጀመረው ከሚል ይልቅ ለኢትዮጵያ ምን ጥቅም ያስገኛል በሚል እየተፈተሸ መልካም የሆነው ሁሉ ጎልብቶ ይሻገራል፤ መልካም ሆኖ ያልተገኘውም ማንም ቢሠራው ጊዜ ራሱ ጥሎት ያልፋል። የትኛውም ሀገር ከስልጣኔ ማማ ላይ የተቆናጠጠው በዚህ መልኩ ነው፤ ሌላ ተዓምር የለም። ሆን ብለን በክፋት ጥሩ ጥሩውን ብንደብቀው በጊዜ ሂደት መገለጡ አይቀርም፤ በተቃራኒው እኛ እስካለን በሚል ያገዘፍነው ጥቅም ሲታጣበት ጊዜውን ጠብቆ ይጣላል። ኢትዮጵያን ስንገነባ ይሄንን ሀቅ መገንዘብ ይገባናል፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን፣

መሪነት በአንድ በኩል ኃላፊነት ለመውሰድ የመቻል፣ በሌላ በኩል በፖለቲካ ትግል ውስጥ የማለፍ፣ አለፍ ሲልም የዕድል ጉዳይ ነው። ሌሎችም ዕድሉ ሲገጥማቸው፣ የፖለቲካው ሂደት ለዚያ ሲያደርሳቸውና ኃላፊነቱን ለመውሰድ ፍላጎትና ቆራጥነት ሲኖራቸው መሪ የማይሆኑበት ምንም ምክንያት የለም።

እየመሠረትነው ያለነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሪነት የፖለቲካ ሂደት ውጤት እንዲሆን የሚያደርግ ነው። የሀገሪቱ ሕግ የሚጠይቀውን ያሟላ፤ በምርጫ ያሸነፈና በፖለቲካ ሥርዓታችን ፍኖት የተጓዘ ኢትዮጵያዊ ሁሉ መሪ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ የሚጠርግ ነው። መሪነት ሥልጣን ሳይሆን ኃላፊነት፤ ገዥነት ሳይሆን አገልጋይነት፤ ድሎት ሳይሆን መሥዋዕትነት ነው።
መሪ ከብዙ ኢትዮጵያውያን መካከል ሕግ እና የፖለቲካ ሥርዓቱ ዕድሉን የሰጠው አንድ ወሳኝ ሰው ነው። መሪዎችን ከዚህ በላይ አድርጎ መመልከት መሪዎችንም ኢትዮጵያንም ይጎዳል። ለመሪዎች ማሰብ፣ ለመሪዎች መጨነቅም መልካምና ተገቢ ነገር ነው። መሪዎችን ከኢትዮጵያ በላይ አድርጎ መመልከት ግን ስሕተት ነው።

ኢትዮጵያ ወደረኞቿን በብዙ ግንባሮች ድል ነስታለች። ለግላዊና ድርጅታዊ ጥቅማቸው ሲሉ ሊያጠፏት የተነሱት ሁሉም አሁን ተረት ሆነዋል። ከታሪክ የማይማሩ ሰዎች ዛሬም ሆነ ወደፊት መነሳታቸው አይቀርም፤ ዳሩ ግን እንደቀደሙት እብሪተኞች ተረስተው ይቀራሉ። በሚታየውም በማይታየውም ዘመቻ ሀገራችን ድል እያደረገቻቸው ትቀጥላለች። ያኔ ጠላቶቿ የሚቀራቸው ግንባር የውሸት ግንባር ብቻ ይሆናል። በእርግጥ ዘመኑም በተወሰነ ሳይረዳቸው አልቀረም።

ዐይናቸው እያየ ልባቸው በሐሰት ፕሮፓጋንዳ የሚዋልልባቸው ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ጥንት ‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው› ይባል ነበር። አሁን ‹ጦር ከፈታው ውሸት የፈታው› ሆኗል። የውሸት ፋብሪካ ከፍተው፣ ውሸት እያመረቱና ውሸት እያሸጉ፣ በጅምላና በችርቻሮ ውሸት ሲያከፋፍሉ የሚውሉ የኢትዮጵያ የጎን ውጋቶች በዝተዋል። ዓላማቸው በሌሎች ግንባሮች ያጡትን ድል በውሸት ግንባር ለማግኘት፤ እግረ መንገዳቸውንም ትርፍራፊ ገንዘብ ለመሰብሰብ ነው።

ለኢትዮጵያ መሞት የማይገኝ ዕድል መሆኑ እንደማይገባቸው ሁሉ፣ ኢትዮጵያን ለመግደል መነሣት የመጨረሻው ርግማን እንደሆነ አያውቁም። ሞት እንደሆን የማይቀር የሰው ልጅ እዳ ነው፤ ከሆነ አይቀር ለታላቋ ሀገር ለኢትዮጵያ ቢከፈል ትልቅ ክብር ነው። ኢትዮጵያ የተገነባችው በኢትዮጵያውያን ሥራ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን መሥዋዕትነትም ጭምር ነው። የሐሰት አበጋዞች በሕይወት ያሉትን ገድለው የሞቱትን ሲያኖሩ ከርመዋል። ነገም አመል ነውና መቀጠላቸው አይቀርም። ኢትዮጵያውያን ግን የሚያዋጣን ለእውነት ስንል መኖር፣ በእውነት መንገድ መመላለስ እና እኛው ራሳችን እውነተኛ ሆነን መቆየት ነው።

የሐሰት ፋብሪካ በጅምላና በችርቻሮ የሚያቀርብልንን የውሸት ፕሮፓጋንዳ በሌለን ጊዜና ገንዘብ እየሸመትን፣ ስንወዛገብ በከንቱ የምንውልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም። እንደ ሀገር ብዙ የቤት ሥራዎች አሉብን። መፈታት የሚገባቸው ቋጠሮዎች፣ መደፈን ያለባቸው ቀዳዳዎች፣ መሞላት የሚገባቸው ጉድጓዶች፣ መጠገን የሚገባቸው ድልድዮች፣ መገንባት የሚገባቸው ሥርዓቶች ተቆጥረው አያልቁም። ያለንን ውድ ጊዜና ሀብት ኢትዮጵያን ለመለወጥ፣ ኢትዮጵያን ለማበልጸግ፣ ኢትዮጵያን ለማስከበር እና ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ብናውለው ይበጃል። ከዚህ የተሻለ ገንዘብና ጊዜያችንን ሊወስድ የሚገባው ምንም ጉዳይ የለንም።

የኢትዮጵያን ወንዞች ለማልማት እኛው ራሳችን የመስኖ ቦዮችን እንቅደድ እንጂ በተቀደደልን የወሬ ቦይ አንፍሰስ። ታላቋን ሀገር በታላላቅ ሐሳቦች ይበልጥ እናተልቃት እንጂ፤ በሐሳብ አንሰን፣ በወሬ ኮስሰን ሀገራችንን አናኮስሳት። ኢትዮጵያ መግዘፍ እንጂ አንሳ መገኘት አይመጥናትም። ለዚያም ሁላችንም በየተሠማራንበት ዘርፍ በዋዛ ፈዛዛ እንቁ ጊዜያችን ማባከኑን ትተን የሰለጠነችና ለሌሎች አርዓያ መሆን የምትችል ኢትዮጵያን ገንብተን ለልጅ ልጆቻችን እናውርስ!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥር 22፣ 2013 ዓ.ም

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.