Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ካሳለፈችው ረጅም የሀገረ መንግስት ግንባታ ውጣ ውረዶች ታሪክ ልትማር ይገባል- ፖለቲከኞች

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ካሳለፈችው ረጅም የሀገረ መንግስት ግንባታ ውጣ ውረዶች ታሪክ ልትማር እንደሚገባ ፖለቲከኞች ተናገሩ።

ከፋና ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት አንጋፋዎቹ ፖለቲከኞች ፕሮፌሰር በየነ ጼጥሮስ እና ዶክተር አረጋዊ በርሄ፥ በዘርፉ ከፍ ያለ ድርሻ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃገር እና የህዝብን ጥቅም ባስቀደመ ግብ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

ሃገራዊ ጉዳዮችን በቅንነትና አርቆ አሳቢነት ለመመልከት ተቀራርቦ መስራት እንደሚጠበቅም ፖለቲከኞቹ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጼጥሮሰ፥ በሃገሪቱ የራቀው ሃገራዊ መግባባት ካለፉ ታሪኮች እንዳንማር አድርጓል ይላሉ።

ፕሮፌሰር በየነ በሃገረ መንግስት ግንባታው ታሪክ የነበሩ እንከኖች እና መልካም ጅማሮዎች ላይ የሚደረሱ የጋራ ስምምነቶች ዜጎች ተስፋ ለሚያደርጓት ጠንካራ ሃገር ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፥ ረጅም ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ዜጎቿ እንደሚመኟት ትሆን ዘንድ ጠንካራ የትብብር ስራዎች ከሁሉም ይጠበቃል ባይ ናቸው።

ለአንድ ጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ ሃገራዊ ጉዳዮችን በቅንነት እና አርቆ አሳቢነት መመልከት ይገባል የሚሉት ፖለቲከኞቹ፥ አለም አቀፍ ተመክሮዎችን ከሃገር ነባራዊ ሁናቴ ጋር አጣጥሞ ተግባራዊ ለማድረግ መስራት ይገባልም ብለዋል።

ለሚፈለገው የዴሞክረሲ እና ጠንካራ ሃገር ግንባታ የፖለቲካ ሃይሎች የሃገር እና የህዝብ ጥቅምን አስቀድመው መስራት እንዳለባቸውም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሊቀመናብርት ተናግረዋል።

ለሚታዮ ሃገራዊ አለመረጋጋት ምክንያት እየሆኑ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባም ተመላክቷል።

ቀዳሚ የሆነን ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንዳለበትም አሰተያየት ተሰጥቷል።

በአወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.