Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካ እንሰሳት ሀብት ዘለቄታዊ ጥበቃና ዋስትና የሚያረጋግጠው ድንጋጌ እንዲፀድቅ ላበረከተችው ሚና እውቅና ተሰጣት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በ5ኛው የተመድ ጉባኤ ወቅት የአፍሪካ የእንስሳት ሀብት ዘለቄታዊ ጥበቃና ዋስትና የሚያረጋግጠው ድንጋጌ እንዲፀድቅ ላበረከተችው ግንባር ቀደም ሚና እውቅና ተሰጣት።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጉባዔ ላይ የአፍሪካን የእንስሳት ሀብት ለመጠበቅና በዘላቂነት ለመጠቀም የሚረዳና “የእንስሳት ሀብቶች ኢንሹራንስ” ረቂቅ ድንጋጌ በ5ኛው የተመድ የአካባቢ ጉባኤ ላይ እንዲፀድቅ ኢትዮጵያ እንድትደግፍ ውይይት ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአፍሪካ ቀዳሚ የቁም እንስሳት ሀብት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ እንድትደግፍ የአፍሪካ ህብረት የልኡካን ቡድን አባላት ከኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ጋር ነው ውይይት ያካሄዱት።

በውይይትና የጋራ ግንዛቤ ላይ በመመስረት ኢትዮጵያ የድንጋጌው መፅደቅ የአፍሪካን ጥቅም ያስጠብቃል ብላ በማመን የካቲት 28 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2022 በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው የተመድ የአካባቢ ጉባኤ ላይ በግንባር ቀደምነት መደገፏን የባለስልጣኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም ለስምምነቱ መፅደቅ ለተጫወተችው የማስተባበር ስራ የአፍሪካ ህብረት የእንስሳት ሀብት ቢሮ ለኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን በመምራት ላይ ለሚገኙት ዶክተር ጌታሁን ጋረደው እውቅና ሰጥቷቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.