Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመፍታት አቅም  እንዳላት ቻይና ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በሀገራት የውስጥ ጉዳይ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን እንደምትቃወም  እና ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውስጥ ችግሯን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ መንገድ መፍታት የምትችል አገር መሆኗን  ቻይና ታምናለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋይግ ይ ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይናው አቻቸው ዋይግ ይ ጋር በሁለትዮሽ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ያብራሩት ምክትል ጠ/ሚ እና ውጭ ጉዳይ ሚ/ር ደመቀ መኮንን÷ የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያ እያሳየ ላለው ድጋፍ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት በተመለከተ ቤጅንግ ያላትን ጽኑ አቋም አድንቀዋል፡፡

ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ቻይና እያበረከተች ላለው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚ/ር  ዋንግ ይ በበኩላቸው÷ ይፋዊ ጉብኝቱ የኢትዮያን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ቻይና ድጋፏን  አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው ያስታወቁት፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ ማለዳ ላይ ነበር ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት።

ከአውሮፓውያኑ 1970 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግኑኝነት የጀመሩት ኢትዮጵያና ቻይና አሁን ላይ በንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ዲፕሎማሲ ጠንካራ ግኑኝነት መመስረት ችለዋል።

በአውሮፓውያኑ ከ2016 እስከ 2018 መካከልም ኢትዮጵያ ከቻይና ያገኘችው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር  ይጠጋል።

በቻይና መንግስት ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሽዬቲቭም በኩልም ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ እና ለአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ከቤጂንግ የብድር ድጋፍ አግኝታለች።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም ቻይና የኢትዮጵያን እውነት በመረዳት ድምፅ በመሆን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ስታደርግም ቆይታለች።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.