Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ፓርላማ ለመቻቻል እና ለሰላም ምክር ቤት አባል ሆነች

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአለም አቀፉ ፓርላማ ለመቻቻል እና ለሰላም ምክር ቤት አባል ሆነች።

የዓለም አቀፉ ፓርላማ ለመቻቻል እና ለሰላም ምክር ቤት አራተኛ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ ያካሄደ ሲሆን፥ ኢትዮጵያም አባል በመሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ስምምነት ፈርማለች።

አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የዓለም ሃገራት እርስ በርስ በቀላሉ የሚገናኙበት አጋጣሚ እየሰፋ መምጣቱን ጠቅሰው፥ አላስፈላጊ ባህሎች በቀላሉ እንደሚዛመቱም ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻርም በወጣቱ ስነ ምግባር ዙሪያ አሁኑኑ መስራት እንደሚስፈልግ አውስተዋል።

የሰላም ጉዳይ በአንድ ድንበር ብቻ ተወስኖ የሚቀር ባለመሆኑ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በሰላም ጉዳይ ላይ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ የማሻሻያ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኗን አብራርተዋል።

የዓለም አቀፉ ፓርላማ ለመቻቻል እና ለሰላም ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አህመድ ቢን ሞሀመድ አል ጃርዋን በበኩላቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለሰላም የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍና እውቅና ለመስጠት፥ 4ኛው ጉባኤ በኢትዮጵያ መደረጉንም አንስተዋል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ የመቻቻልና የሰላምና ዓለም አቀፍ የፓርላማ ምክር ቤት 60 ሃገራትን በአባልነት ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያም ከምክር ቤቱ የቀረበላትን የአባልነት ጥያቄ ተቀብላ እንደተቀበለች መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.