Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ሰላም የምትመኝ ብቻ ሳትሆን የልጆቿን ህይወት ጭምር እየገበረች ሰላማቸውን የምትጠብቅ ናት – አምባሳደር ሬድዋን

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ሰላምና ብልፅግና የምትመኝ ብቻ ሳትሆን የልጆቿን ህይወት ጭምር እየገበረች ሰላማቸውን የምትጠብቅ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳር ሬድዋን ሁሴን ገለፁ።

የአውሮፓውያኑን ዘመን አቆጣጠር ለሚያከብሩ ባስተላለፉት የመልካም አዲስ ዓመት መልዕክት በተጋጩ ጊዜም ሌት ከቀን ለማስታረቅ የምትታትር ሀገር ናት ብለዋል።

በቅርቡም የሱዳንን ሀይሎች በማግባባት የተሳካ ሽምግልና ማከናወኗ ሱዳናውያን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ጭምር ያረጋገጡት እውነታ መሆኑን በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ወዝግብ ከመቶ አመታት በላይ የዘለቀ፣ በመግባባት ይቋጭ ዘንድም የጋራ ኮሚሽንና የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቶ አንድ ጊዜ በኢትዮጵያ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሱዳን በኩል በተፈጠሩ ሁኔታዎች ብቻ ሳይቋጭ የሰነበተ መሆኑን አስታውሰዋል ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በኩል ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ቁርጠኝነት እንዳለ ሱዳናውያን በግልፅ ያውቃሉም ብለዋል።

ሆኖም በቅርቡ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ በማተኮር ሠራዊቷን ወደ ሰሜን ስታዞር የሱዳን ሀይሎች ስፍራውን ለመቆጣጠር ባደረጉት እንቅስቃሴ ሳቢያ የተፈጠረው አለመግባባት በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል ወደ ግጭትና ጦርነት እንዲያመራ ማን ከበሮ ሲደልቅ እንደነበር ግን የአደባባይ ሚስጥር እንደሆነ አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።

ሰሞኑን አምባሳደር ዲና ለብዙኃን መገናኛ መግለጫ በሰጡበት ወቅት አንዳንድ ሃይሎች ሱዳንን ከወዳጅ ሀገር ኢትዮጵያ ጋር በድንበር ውዝግብ ሰበብ ግጭት ውስጥ እንድትገባ በመገፋፋት፣ ቀጠናውን በማተራመስ የውስጥ ችግሮቻቸውን አቅጣጫ ለማሳት በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ገልፀው እንደነበርም አስታውሰዋል።

ኬንያ ፣ ጂቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን ወይም ሶማሊያ እኛን ይሆን? ብለው አልተጨነቁም፣ አልጠየቁም ያሉት ሚኒስቴር ዲኤታው ከግብፅ በኩል በእርግጠኝነት እኛን ማለት ነው የሚሉ ይፋ ድምፆች እየተደመጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ስም ባንጠቅስም የምንሰራውን እናውቃለንና በትክክል እኛ ነን ካሉ ኢትዮጵያ ግብፅን ወክላ ስለ ግብፅ ልትከራከር እንዴት ይቻላታል ሲሉም ጠይቀዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናልhttps://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.