Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ወደ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ወደ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱና በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት እንዲያከብሩ ጥሪ አቀረበች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በህዳሴ ግድብ ላይ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት እየተካሄደ ያለውን ድርድር በተመለከተ ለፀጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ የኢትዮጵያን አቋም አሳውቀዋል፡፡

በዚህም የምክር ቤቱ አባላት ሃገራቱ ወደ ሶስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱና በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በደብዳቤያቸውም በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ሂደት የፀጥታው ምክር ቤትን መርሆዎች መሠረት ያደረገና ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን የሚያፈላልግ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጅ ግብጽና ሱዳን በቅን ልቦና እየተደራደሩ አለመሆኑን በመጥቀስ፥ የሚያግባባና አሸናፊ ወደ ሆነ ውጤት ለመድረስና አስፈላጊ ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም ሃገራቱ ድርድሩን “መበጥበጥና ማበላሸትን” ምርጫ ማድረጋቸውን እና ጉዳዩን “ዓለም አቀፋዊ ይዘት” በማላበስ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለመክተት እየሞከሩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ እና አሁን ላይ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚል መርህን በመከተል ጉዳዩን ዳር ለማድረስ ለሚያደርጉት ጥረት ያላትን ምስጋና እና አድናቆትም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የግድቡ ውሃ ሙሌት ቀደም ብሎ መረጃ ለመለዋወጥ ያሳየችውን ተነሳሽነት በማስታወስ ሃገራቱ ውድቅ ያደረጉበትን መንገድም አንስተዋል፡፡

ሃገራቱ በህዳሴው ግድብ ላይ የያዙትን ፍትሃዊ አቋም ለማሳካትና በውሃ ፍሰት አጠቃቀሙ ሁሉን አቀፍ አስገዳጅ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሄዱበት መንገድ ተቀባይነት እንደሌለውም አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያም የሶስቱ ሃገራት ለገቡት የመርህ ስምምነት ያላትን ተገዥነት በማንሳትም፥ ግብጽና ሱዳን የገቡትን የመርህ ስምምነት በመተው ማፈንገጣቸውንም ነው በደብዳቤው ያወሱት፡፡

ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለመክተት የሚደረግ ሙከራም ሆነ ከአፍሪካ ህብረቱ መር ሂደት ማፈንገጥም በሃገራቱ መካከል ያለውን መተማመን የሚያፈርስና እምነት የሚያሳጣ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.