Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የሆነ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን የሚያቅብ ማናቸውንም ዓይነት ስምምነት አትፈርምም – የውሃ፣መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣2013 (ኤፍ ቢ ሲ)- በኮንጎ ኪንሻሳ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ስለሚቀጥልበት ሁኔታ ለመመካከር የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ አወንታዊ ውጤት እንዳይኖረው ግብጽ እና ሱዳን እንቅፋት ሆነዋል ሲል የውሃ፣መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሁለቱ ሀገራት ስምምነት ሳይደረስ ግድቡ መሞላት የለበትም በሚል የሚቀርብ አቋም የህግ መሰረት የሌለው እንዲሁም ኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብሏል በመግለጫው፡፡

የግድቡ አሞላል እና ተያያዥ የውሃ አለቃቀቅ ላይ የሚደረግ ስርዓት ላይ ለመስማማት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ዝግጁ ብትሆንም ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር እና ውጤት የኢትዮጵያን የውሃ ድርሻ የሚገድብ እና አለን የሚሉትን የውሃ ክፍፍል የሚያጸና አስገዳጅ ስምምነት ካልተደረገ የሚል ግትር አቋም ይዘዋል፡፡

በስብሰባው ሶስቱ ታ ዛቢዎች (ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት) በታዛቢነት እንዲቀጥሉ ሰምምነት የተደረሰ ሲሆን፣ በሚኖራቸው ሚና ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ሶስቱ ሀገራት በጋራ ስምምነት ሲጠየቁ ብቻ ሃሳብ ለማቅረብ ለመፍቀድ ኢትዮጵያ ተስማምታለች፡፡

ግብጽ እና ሱዳን ታዛቢዎቹ ከአፍሪካ ህብረት እኩል ተሳትፎ የማድረግ ሚና ሊሰጣቸው ይገባል በሚል ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ይህ የሁለቱ ሀገራት አካሄድ የአፍሪካ ህብረትን ሚና የሚያሳንስ ነው ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የሆነ የአሁኑ እና የወደፊት በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን የሚያቅብ ማናቸውንም ዓይነት ስምምነት አትፈርምም ነው ያለው ሚኒስቴሩ፡፡

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር የቀረበውን ረቂቅ መግለጫ ኢትዮጵያ ለመቀበል መስማማቷን ስትገልጽ፣ ግብጽና ሱዳን በሁለቱ ቀናት ውይይት ያልተነሱ ጉዳዮች ካልተካተቱ በሚል አንቀበልም በማለት ድርድሩ አውንታዊ ውጤት እንዳይኖረው እንቅፋት ሆነዋል፡፡

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሰብሳቢ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሼሲኬዲ እና ቡድናቸው ድርድሩን ለማስቀጠል ያሳዩትን ብርቱ ጥረት የኢትዮጵያ መንግስት በከፍተኛ አክብሮት ይመለከተዋል ብሏል የውሃ፣መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመግለጫው፡፡

ኢትዮጵያ የድርድሩ ሒደት የሀገራቱን ሙሉ ባለቤትነት በሚያረጋግጥ እና የአፍሪካን ህብረት የማስተባበር ሚና በተሟላ አኳኋን የሚያስጠብቅ የሶስትዮሽ ድርድር ለመከተል ዝግጁ ናትም ብሏል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.