Fana: At a Speed of Life!

ኢንስቲትዩቱ በተያዘው ዓመት ማብቂያ የሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም ዓቀፉ የሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በዚህ ዓመት መጨረሻ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መርሃ ግብር እንደሚጀምር አስታወቀ።

የሚጀመረው የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መርሃ ግብር በሠላምና ግጭት አፈታት ዘዴ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

የተቋሙን የትምህርት አሰጣጥ ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በኢንስቲትዩቱ ቅጥር ግቢ የማረጋገጫ አውደ ጥናት ምክክር እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ከመከላከያና ከፖሊስ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከአለም ዓቀፍ የሠላምና ደህንነት ጥናት እና ከጦር ኮሌጅ፣ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች አገራት የተወከሉ መኮንኖች ተሳትፈዋል።

የዓለም ዓቀፉ የሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ ÷ኢትዮጵያ የሚሰጣትን የሠላም ማስከበር ግዳጅ በእውቀትና ክህሎት የተገነባ ለማድረግ በኢንስቲትዩቱ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መስጠት አስፈልጓል።

ለተቋሙ የሚሰጡት የሠላም ማስከበር ግዳጅና ኃላፊነት እየሰፋ በመምጣቱ ከዚህ ቀደም ለሠላም አስከባሪ አባላት ሲሰጡ የነበሩ አጫጭር ስልጠናዎች ብቻ አቅምን ለመገንባት በቂ እንዳልነበሩ ገልጸዋል።

እየሰፋ የመጣውን ግዳጅና ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት የትምህርት ደረጃን ከፍ በማድረግ በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያለውን ተሳትፎ ከወታደር ባለፈ በኃላፊነት ቦታዎች በቂ እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያን የሚወክሉ ሰዎች እንዲሩ ማድረግ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዓለም ዓቀፍ ሠላምና ደህንነት ጥናት ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዮናስ አዳየ÷ “ሠላም ማስከበር ሊቆም የሚችል ጉዳይ ባለመሆኑ የግጭት ምንጮችን፣ መከላከያ መንገዶችን፣ የማኅበረሰብ ማስታረቂያ መንገዶችን ማወቅ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የሁለተኛ ዲግሪ ለመጀመር ማሰቡም ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣይ በተቋሙ ለሚማሩ የቀጠናውና ሌሎች አፍሪካዊያን እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ በማድረግ ስራቸውን በሳይንሳዊ ዘዴ እንዲመሩ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የሠላም ማከበር ሂደት በእውቀትና ክህሎት የተመሰረተ ለማድረግ ተቋሙ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መጀመር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

የትምህርት ፕሮግራሙ ከጃፓን መንግስት ጋር በመተባበር እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።

በተያዘው ዓመት መጨረሻ አካባቢ በመጀመሪያው ዙር ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች እንደሚገቡም  ታውቋል።

በቀጣይ የምስራቅ አፍሪካና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎችን ወደ ተቋሙ ለማምጣትም ታቅዷል።

ይህ ተግባራዊ ሲደረግ ኢትዮጵያዊያን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ተማሪዎች ጋር የእውቀትና ክህሎት ልምድ በመውሰድ የቀጠናው ማኅበራዊ ትስስር እንደሚጠናክር ተነግሯል።

ኢንስቲትዩቱ ወደፊት በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ሊሰጣቸው ያሰባቸውን የትምህርት ይዘቶች በሚመለከት የመነሻ ጹህፍ ቀርቦ ውይይት መደረጉን ኢዜአ ዘግቧል።

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.