Fana: At a Speed of Life!

ኢዜማ 138 ቁልፍ ግቦችን የያዘ የቃል ኪዳን ሰነድ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢዜማ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ችግር ያቃልላሉ ያላቸውን 138 ቁልፍ ግቦችን የያዘ የቃል ኪዳን ያለውን ሰነድ ዛሬ ይፋ አደረገ፡፡

ፓርቲው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለመዲናዋ ነዋሪዎች ሊሰሩላቸው ይገባሉ ብሎ የለያቸውን 138 ቁልፍ ግቦች አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት ‘‘ኢዜማ እውነተኛ ፌዴራሊዝም መሰረቱ ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ነው’’፡፡

አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ከተማ ብትሆንም በቅድሚያ ለሚኖሩባት ዜጎች ምቹ ሆና እንድትገኝ ማድረግ ይገባናልም ብለዋል።

“ፓርቲው ከሕዝቡ ጋር ወርዶ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት የነዋሪዎቿ ችግር ስር የሰደደ መሆኑን ለይተናል፤ ለዚህ የሚመጥን የአምስት ዓመት 138 ቁልፍ ግቦችን የያዘ የቃል ኪዳን ሰነድም አዘጋጅተናል” ነው ያሉት።

አዲስ አበባን የከተማዋ ነዋሪ የሆነ፣ የሕዝቡን ችግር የተረዳና በሕዝብ የተመረጠ ማንኛውም ግለሰብ ማስተዳደር ይችላልም ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የኢዜማ ዕጩ አቶ ክቡር ገና በመዲናዋ ስር የሰደደውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በአምስት ዓመት ውስጥ በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች የሚተላለፍ ከ200 ሺህ ያላነሰ የጋራ መኖሪያ ቤት እንደሚገነባ ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የከተማ አስተዳደሩ በሚያወጣው የጥራት ደረጃ መሰረት የቀበሌ ቤቶችን ለሚኖሩባቸው ሰዎች ቅድሚያ በመስጠት በሁለት ዓመታት ውስጥ በሽያጭ እንዲዘዋወሩ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

የዜጎችን ገቢ ከፍ፤ ወጪያቸውን ዝቅ የሚያደርጉ አሰራሮች በመተግበር የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር፣ የከተማዋን ሠላምና ጸጥታ የሚያስጠብቅ ጠንካራ የደህንነት መዋቅር መዘርጋት፣ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ዘመናዊ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትና ሌሎችም ከተማዋን የሚመጥኑ አሰራሮች ይተገበራሉ ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

የኢዜማ የየካ ክፍለ ከተማ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕጩ አቶ አሮን ሰይፉ በበኩላቸው፤ በከተማዋ ጥራቱን የጠበቀ የማኅበራዊ ዘርፍ አገልግሎት መስጠት ቀዳሚ ስራችን ይሆናል ነው ያሉት።

ከእነዚህ መካከል የመምህራንን አቅም በመገንባት ብቁ ተማሪዎች ከማፍራት በተጨማሪ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግን ጠቅሰዋል።

ደረጃቸውን የጠበቁ የሕክምና ተቋማት በፍትሃዊነት ማስፋፋትና የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ማቃለልም በመጭው አምስት ዓመት ለሕዝቡ የምንገባው ቃል ነው ብለዋል አቶ አሮን።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.